የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ

"ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ሕይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ውስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነው" የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ

ከሁሉ አስቀድመን በመቐለ ከተማ በጠራራ ፀሐይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ በታጠቁ ኃይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን እየገለጽን፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳድ የትግራይ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ገዳይና አሰከፊ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሕዝብ ጋር በመሆን የመከላከል እና ሕዝብን የማዳን ሥራ እተሰራ ይገኛል።

በዚሁ ሁኔታ መንግሥትና ፓርቲያችን ዘርፈ ብዙ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወንና በመተግበር ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጉልህ ዘርፈ ብዙ አወንታዊ ውጤቶች ባሻገር የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች አብይ ፈተና ሆነዋል።

በተለይም በግጭት አትራፊዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚፈጥሩትና በሚቀሰቅሱት ግጭቶችና ሁከቶች ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጥፍ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ድርጊት ለሕዝቦች ሆነ ለአገራዊ አንድነት የማይበጅ እንዲሁም አሳዛኝ ድርጊት ነው።

ሕዝባችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግሥት አመራሮችና ሰራተኞች ሕዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደምንገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።

ሆኖም መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም የሥጋት ደረጃና መጠኖችን በመመርመርና በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ፀረ ለውጥና ጸረ-ኢትዮጵያዊያን ኃይሎች ሆን ብለውና አቅደው በተሳሳተ መንገድ ሕዝቡን በማደናገርና ወደ ጥፋት ጎዳና ለመምራት እየሰሩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ይህንን አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ለግላዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ለማሟላት ሕዝብንም ሆነ አገርን የሚጎዱ አስነዋሪና አጸያፊ ተግባሮችን በመፈጸም ላይ እንደሚገኙ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰነባብቷል።

የትግራይ ሕዝብ የቅርብ ሆነ የሩቅ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ጭቆናንም ሆነ አፈናን የሚጸየፍ ለኢትዮጵያ አንድነት መሥዋእት የከፈለ ሕዝብ ነው።

በትግሉና በመስዋእትነቱም ለመላው የአገራችን ሕዝቦች ጉልህ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ የተወጣና በመወጣትም ላይ ያለ ሕዝብ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋእትነት የሰላምና ዴሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ ዓለም
ብቻ እየሆነበት መጥቷል።

ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ሕይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ውስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነው።

በሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነው የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የኀዘንና ውጥረት ድባብ ውስጥ ይገኛል። ይህ ክቡር የሰው ሕይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ጸጥታን በሕግ አግባብ ለማስጠበቅ ሃላፊነት በተሰጠው የጸጥታ አካል የተፈጸመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል።

ይህም ድርጊት ብዙ መስዋእት ለከፈለ የማይገባው ነው። በመሆኑም የወጣቱ ግብረመልስም በክልሉ ሰላምና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የኔ ጉዳይ ነው የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጐቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልጽ አሳይቷል።

እንደሚታወቀው በአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማሰፈጸም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና በሕግ የማስከበር ተግባር ላይም የጸጥታ አካላት የላቀ ሰብአዊነት፣ ታጋሽነትና፣ ፍፁም ሕዝባዊነትን የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል።

የዲሞክራሲና የተሻለ የሰብአዊ መብት አያያዝ ልምድ ጉዳይ ከአስተምህሮት ስርፀትና ግልጽ ተጠያቂነትን ከማስፈን አሰራር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ሲሆን፤ ዜጎች በመንግሥታቸው የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ክስተቶች አፈናና ግልጽ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል።

በተለይም እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ሕይወታቸውን እስከመቅጠፍ የደረሰ የኃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው።

ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው እርምት እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

ይህ እኩይ ተግባር በተለይ በክልሉ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ፣ ይህን መሰል የአፈና ተግባር የክልሉ ወጣት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ አጥብቆ እንዲታገለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በአጠቃላይ አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉና በአገር ደረጃ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ድጋፉ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

"ወደ ሕዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ" እንደሚባለው፣ የገዢዎች የውድቀት ምልክት የሚጀምረው ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመሩ እለት ነው። ስለሆንም በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ ባጋጠመው ክስተት፣ በክልሉ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የክልሉ ገዢ ፓርቲና መንግሥት አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲመረምር አስገዳጅ ማንቂያ ደወል ነው። የትግራይ ብልጽግና ፓርቲም ጉዳዩን በአፅንኦት እንደሚከታተለውና ለሚመለከታችሁ ሁሉ በጥብቅ ያሳስባል።

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም የትግራይ ወጣት እና ለውጥ ፈላጊ ኃይል ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጋር በመሆን የለውጥ ሂደቱን እንዲያፋጥኑ ከፓርቲያችን ጋር እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ፓርቲያችን የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚገባውን ጥቅም እንዲረጋገጥ እና አገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ይሰራል። በጥቂት ገዥ የህወሓት ቡድን በተለይ በዝምድና እና ጥቅም ትስስር እንዲሁም በሥልጣን ጥማት ምክንያት ትግራይን ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ለመነጠል የሚደረግ ሥራም ሆነ ሴራ በጥብቅ የምንታገለውና የምናወግዘው መሆኑን በጥብቅ እናሳውቃለን።

በመጨረሻም ለሟች የዘለዓለም እረፍት፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ከልብ እንመኛለን።

ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ግንቦት 11/2012

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!