ብልጽግና

ብልጽግና ፓርቲ

ሕወሓት አሁንም የትግራይ ሕዝብ የለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የቀድሞ የማታለል ሴራውን እየተገበረበት ይገኛል

እኛ የትግራይ ተወላጅ የሆንን የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፣ ባለፉት ቀናት ስለአጠቃላይ የአዲስ አበባ የፓርቲያችን መዋቅር እንዲሁም ኮቪድ 19፣ የምርጫ መራዘምና የሕግ አማራጮች በሚል ርዕስ ስናደርግ የነበረውን ውይይት በማጠናቀቅ የሚከተለውን የጋራ አቋም መግለጫ አውጥተናል።

ፓርቲያችን ብልጽግና የመላው ኢትዮጵያውያን ፓርቲ ሆኖ፣ ሁሉንም ሕዝቦች በፍትሐዊነትና በእኩልነት የሚያሳትፍ አደረጃጀት ፈጥሮ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ይታወቃል።

እኛ በተለያየ የአመራር ቦታ ያለን የቀድሞ የሕወሓት አባላት፣ በብልጽግና ፓርቲ ታቅፈን ለመንቀሳቀስ እና የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ካለን ፅኑ ፍላጎት በገዛ ፍቃዳችን ስንቀላቀል፣ ፓርቲያችን መላውን ሕዝባችንን በተለይም ባለፉት አመታት ምንም ሳይጠቀም እንደተጠቀመ ተቆጥሮ በስሙ ሲነገድበት የነበረውን የትግራይ ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልና የሕዝቡንም ቀጣይ እጣ ፋንታ ብሩህ ማድረግ እንደሚችል ካለን ጠንካራ ልባዊ እምነት የተነሳ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ለመብቱ እና ለነፃነቱ ውድ ዋጋ የከፈለ፣ ከኢትዮጵያዊ ወንድም እና እኅቶቹ ጋር በጋራ መኖር የሚፈልግ ታላቅ ሕዝብ ነው። ነገር ግን ይህ ትግሉ በጥቂት የራሳቸውን የግል ሥልጣን ለማደላደል በሚፈልጉ ቡድኖች ታጥሮ፣ የታገለለትን መብት በሚገባ ሳይጎናፀፍ ዛሬም ታፍኖ እኔ አውቅልሃለው በሚል መርህ ከሌሎች ወንድሞቹ እና እኅቶቹ ጋር የመገለል ስሜት እንዲያድርበትና በጥርጣሬ እንዲኖር እየተደረገ ይገኛል።

የትግራይ ሕዝብ ከታገለላቸው ዓላማዎች አንዱና ዋነኛው ሕብረ-ብሔራዊ ፌደራሊዝም ሥርዓት በአገራችን እውን እንዲሆን ነው። ነገር ግን እነዚህ ጥቂት እኩይ አላማ ያላቸው ቡድኖች “ብልጽግና አሃዳዊ ሥርዓት ነው!” የሚል የተዛባ ፕሮፖጋንዳ እየነዙ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ወገኖቻችንን እያሳሳተ ይገኛል። ሆኖም ብልጽግና ለእውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በመከባበር እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ የሕዝቦች ግንኙነት ለማጠንከር የሚሠራ ፓርቲ እንጂ በፌደራሊዝም ስም የጥቂቶችን ፍላጎት ለማራመድ የማይሠራ ፓርቲ ነው።

ሕወሓት አሁንም የትግራይ ሕዝብ የለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የቀድሞ የማታለል ሴራውን እየተገበረበት ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት ሕብረተሰብ እና መንግሥት በአገራችን የተከሰተውና ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ በሚደረግበት “ምርጫ ካልተደረገ የሚል ግትር አቋሙም ለሕዝቡ ደኅንነት ደንታ እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል።

ምርጫ የሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብት መሆኑን እናምናለን። ነገር ግን የሕዝብን ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት ስለሚገባ፣ በፓርቲያችንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ መራዘም የተያዘውን አቋም ተገቢና ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን እናምናለን። ቀጣይ እርምጃዎችም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባከበረ መልኩ መካሔድ እንደሚኖርበትም የማያወላላል አቋም አለን።

በነበረን የውይይትና የምክክር መድረክም የሚከተለውን ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

1ኛ መንግሥት የምርጨውን መራዘም አስመልክቶ እየሔደበት ያለው ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ የመፍትሔ አቅጣጫ፤ የሕዝቡን ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ፤ አሁን የተጋረጡብንን አደጋዎች እንደ አገር ትኩረታችን ሳይዘነጋ እንድንከላከል የሚያግዝ በመሆኑ፣ የምንደግፈውና ለተግባራዊነቱም ከፓርቲያችን እና ሕዝባችን ጎን በመሆን የምንታገል መሆኑን እንገልፃለን።

2ኛ በክልል ደረጃ ምርጫ ማካሔድ የማይቻልና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው። ስለሆነም ሕወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ አካሂዳለው ብሎ መነሳቱ ፍጹም ሕገወጥና የአገሪቱን ሕጎች መናድ በመሆኑ በአስቸኳይ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እናሳስባለን።

3ኛ ብልጽግና የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ነው። ይህ ፓርቲ የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ወንድምና እኅት ሕዝቦች በጋራ የልማት እና የእውነተኛ ዲሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራ ይገኛል። ነገር ግን በተለመደ የማጠልሸት ተግባራቸው ብልጽግና የትግራይን ሕዝብ እንደሚጠላ በማስመሰል የራስን ሥልጣን ለማቆየት የሚያደርጉትን ጥረት በመቃወም የብልጽግና ጉዞው ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

4ኛ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም እኅቶቹ ጋር በጋራ መኖር የሚያውቅ፣ ለኢትዮጵያዊ አንድነት ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው። በመሆኑም ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላምና በመከባበር በወንድማዊ ስሜት ሆነን፣ አብሮነታችንንና አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴያችንን እንድናፋጥን እየጠየቅን፣ ይህን ከፋፋይ ተግባር በጋራ ሆነን እንድንታገለው ጥሪ እናቀርባለን።

5ኛ በመጨረሻም፣ የህዳሴ ግድባችን ለአገራችን የብልጽግና ጉዞ ወሳኝና እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ እኛ የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በግድቡ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውጫዊ ጫናና ጣልቃ ገብነት በፍጹም የማንቀበለውና፤ ለግድቡ እውን መሆን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።

ግንቦት 2012
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ