ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)

ገዢው ፓርቲ ያለበቂ ውይይት እና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ እሄደበት ያለው ጥድፊያ በአስቸኳይ ይቁም!

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

አንኳር

- ቴልኮም በ21ኛው ክፈለ ዘመን የፋይናንስ ሥርዓት መተግበሪያ፣ የመገናኛ ብዙኃን የደም ቧንቧ፣ ከፍተኛ የሆነ አገራዊና ወታደራዊ መረጃዎችን ማስተላለፍያ፣ ከመሪዎች ጀምሮ ከፍተኛ የአገር አስተዳደሪዎች መረጃ መቀባበያ፣ ለደህንነት ሥራዎች መረጃ ማግኛ ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጦር መሳሪያና ጦር ሜዳ ሆኖ ተመልከተናል። ከዚህ ባለፈ ኢንዱስቲሪው ብዙ ሌሎች ኢኮኖሚ ዘርፎች ተወዳደሪነታቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነ ግብዓት እና ለአገራችን የወደፊት እድገት ያለውን አቅም መገነዝበ ተገቢ ነው።

- መንግሥት ይህን ከሚያስገኘው ትርፍ በዘለለ ለፈጠራ እና ምርምር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ተወዳዳሪነት ዋነኛ ሞተር የሆነን የቴሌኮም ኢንደስትሪ እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፍያ ብቻ በማየት ለውጪ ድረጅት ለመሸጥ የጀመረው መንገድ ፍፁም አደገኛ እና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፣ መንግሥትም ቆም ብሎ ማስብ አለበት ብለን እናምናለን።

- ቴሌኮም ሲሸጥ ገዢዎቹ ከገዙት መጠን በላይ ተፅዕኖ በማሳደር የድርጅቱና የተግባሩ ባለቤቶች ለመሆን ይጥራሉ። ይህ በብዙ አገራት የታየ ክስተት ነው። የገዥዎች ዓላማና ፍላጎት ትርፍ በመሆኑ ድርጅቱ የሚሰማራባቸው ተግባራት ሁሉ ወጪ የሚቀንሱ፤ ትርፍ የሚያጋብሱ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ይህም በሠራተኛ ቅጥር፤ በደመወዝ፤ በአስተዳደር ላይ አንዳንዴም በታሪፍ ላይ ሊንፀባረቅ ይችላል።

- ከኮቪድ 19 በኋላ ዓለም ወደምን ዓይነት ኢኮኖሚዊ ሥርዓት እያመራች እንደሆነ መገመት በሚያዳግትበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ከትርፉ ጉዳቱ ያመዝናል። የሚወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች አሁን ካለንበት ችግር የሚያወጡን ብቻ ሳይሆኑ የወደፊቱንም ትውልድ የምጣኔ ሀብት እና የማኅበራዊ ነፃነቱን በምንም ዓይነት መልኩ አደጋ ላይ የማይጥሉ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት።

- ከዚሁ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የቴለኮም የአከሰዮን ድርሻ ዋጋ ዓለም ላይ በእጅጉ ወርዷል። በሁሉም የገበያ መረጃ ቋቶች ላይ ማየት እንደሚቻለው ወደ 40 ገደማ የሚሆኑ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የቴሌ ካምፓኒዎች የአከሰዮን ደርሻ ዋጋቸዉ ቀይ ዞን ውስጥ ገብቷል። በዚህ ወቅት የሚደረግ ፕራይቬታይዜሽን የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ መጠን የቱንም ያህል ቢሆን ገዥ ያጣ ንብረት በሚጣልበት ዋጋ እንደተሸጠ ይታሰባል።

- በተጨማሪም ሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ከገባው ቃል በተቃራኒ ያለበቂ ውይይት እና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ እሄደበት ያለው ጥድፊያ ከዚህ ቀደም በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እየተመከሩ የምጣኔ ሀብት ሪፎርም ያካሄዱ እና በዚያ ምክንያት የተቋሞቹ የረጅም ጊዜ ጥገኛ ሆነው ሉዓላዊነታቸውን ያጡ አገራት ከሄዱበት መንገድ ጋር ተመሣሣይ ነው።

- ገዢው ፓርቲ ይህን በአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ስትራቴጂክ ሴክተር ላይ ሕጋዊ ቅቡልንትን ሳያረጋግጥ፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ቅድሚያ ሳይሰጣቸው፤ በቂ ጥናት ሳይደረግ እና የንብረቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብና ወኪሎቹ ሳይመካከሩ ከየትኛውም ኃይል ይሁንታን ሳይጠብቅ በውጭ ጫና እና ማባበያ የወሰነውን ውሳኔ በመቀልበስ የኢቲዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ እየሄደበት ያለውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም እናሳስባለን።

- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ የያዘ በምጣኔ ሀብት እና በአይ.ሲ.ቲ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያዘጋጁት ምጥን ፖሊሲ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ኅብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ እንዲያገኝ እና ከመንግሥት ግልጽነትን እንዲጠይቅ የሚገፉ ውይይቶች በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ይደረጋሉ። በምጥን ፖሊሲው ላይ የተለያዩ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የዙም ዌቢናርም እንደምናዘጋጅ በዚህ አጋጣሚ አስቀድመን እናሳውቃለን።

ያለበቂ ውይይት እና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ እሄደበት ያለው ጥድፊያ በአስቸኳይ ይቁም!

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ቴሌኮም የዓለም ኢኮኖሚ ሞተር ከሆነ ሰነበት፣ አገራችን ኢትዮጵያም እድገቱ እንደበለፀጉት አገራት አይድረስ እንጂ ዘርፉን ከተቀላቀለች 100 ዓመት አለፋት። ዛሬ ላይ የቴሌኮም ጉዳይ ከኢኮኖሚ ማዕከልነት አልፎ የአገር ደህንነት ጉዳይ (national security issue) ነው። ቴሌኮም በ21ኛው ክፈለ ዘመን የፋይናንስ ሥርዓት መተግበሪያ፣ የመገናኛ ብዙኃን የደም ቧንቧ፣ ከፍተኛ የሆነ አገራዊና ወታደራዊ መረጃዎችን ማስተላለፍያ፣ ከመሪዎች ጀምሮ ከፍተኛ የአገር አስተዳደሪዎች መረጃ መቀባበያ፣ ለደህንነት ሥራዎች መረጃ ማግኛ ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጦር መሳሪያና ጦር ሜዳ ሆኖ ተመልከተናል። ከዚህ ባለፈ ኢንዱስትሪው ብዙ ሌሎች ኢኮኖሚ ዘርፎች ተወዳደሪነታቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነ ግብዓት እና ለአገራችን የወደፊት እድገት ያለውን አቅም መገነዝበ ተገቢ ነው። በዘርፉ እምርታ ካሳዩት አገራት አንዷ የሆነችው አሜሪካ እ.አ.አ. በ1982 ብሔራዊ የቴሌኮሚኒኬሽን ደህንነት አማካሪ ኮሚቴ (National Security Telecommunication Advisory Committee) በሚል በሮናልድ ሬገን በተቋቋመ ቡድን የተጀመረው ቴሌኮምን የአገር ደህንነት ማዕከል አድርጎ የመጠቀም ጅማሮ ዛሬም ድረስ ቀጥሎ አለ። የሌሎች አገራትም ልምድ የሚያሳየን የቴሌኮም ሴክተር የአገር ደህንነት ለማጠንከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው።

መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን 40% ድርሻ ለድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች (Multinational Corporations) ለመሸጥ ድርጅቱን የመገመት ሥራ እንዲከናወን እያደረገ እንደሆነ እና ሽያጩን የሚያማክሩ አማካሪ ድርጅቶችን እየመረጠ እንደሚገኝ አውቀናል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መንግሥት ይህን ከሚያስገኘው ትርፍ በዘለለ ለፈጠራ እና ምርምር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ተወዳዳሪነት ዋነኛ ሞተር የሆነን የቴሌኮም ኢንደስትሪ እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፍያ ብቻ በማየት ለውጪ ድረጅት ለመሸጥ የጀመረው መንገድ ፍፁም አደገኛ እና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፣ መንግሥትም ቆም ብሎ ማስብ አለበት ብሎ ያምናል።

ኢትዮ ቴሌኮም መሸጥ እና በግል ይዞታ መተዳዳር አለበት የሚሉ አካላት የሚያነሷቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው። በዋናነት በተለይም ከመንግሥት በኩል የሚነሳው ምክንያት አገልግሎቱን ለማዘመን እና ጥራትን ለማሻሻል የሚል ነው። በተጨማሪም አገራችን ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ሥራአጥነት ለመቅረፍም ነው የሚል ምክንያትም ይነሳል።

ኢትዮ ቴሌኮምን ከላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶችንም በዘለለ እና በበለጠ ሁኔታ አሁን በጥድፊያ እንዳይሸጥ ምክንያት የሚሆነው ከላይ እንደተገለፀው ስትራቴጂካዊ ተቋም መሆኑ ነው። የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴሌኮም ዘርፍ እንደጥንቱ በመገናኛና መረጃ አስተላላፊነት (ICT) ብቻ ሳይወሰን ወታደራዊ፣ ፋይናንስ መገናኛ-ብዙኃንና የፈጠራ ሥርዓቱን የመቆጣጠር ሚናው እየጎላ መጥቷል።

የተቋሙ ባለቤትነት በከፊልም ቢሆን በግል ይዞታነት ሲወሰድ የመንግሥት እነዚህን ለአገራችን ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን መቆጣጠር አቅምም አብሮ መቀነሱ አይቀሬ ነው። ቴሌኮም ሲሸጥ ገዢዎቹ ከገዙት መጠን በላይ ተፅዕኖ በማሳደር የድርጅቱ ብሎም የተግባሩ ባለቤቶች ለመሆን ይጥራሉ። ይህ በብዙ አገራት የታየ ክስተት ነው። የገዥዎች ዓላማና ፍላጎት ትርፍ በመሆኑ ድርጅቱ የሚሰማራባቸው ተግባራት ሁሉ ወጪ የሚቀንሱ፤ ትርፍ የሚያጋብሱ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ይህም በሠራተኛ ቅጥር፤ በደመወዝ፤ በአስተዳደር ላይ፥ በተደራሽነት ዙሪያ አንዳንዴም በታሪፍ ላይ ሊንፀባረቅ ይችላል።

ኢትዮ ቴሌኮም ሃገራችን ውስጥ ካሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች በእጅጉ አትራፊው ነው። በየዓመቱ በርካታ ቢሊዮን ብሮችን አትርፎ ወደመንግሥት ካዝና የሚያስገው ይህ ድርጅት ዘንድሮ በስድስት ወር ብቻ ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ አትርፏል። ይህንን ድርጅት ወደግል ማዛወር ከተቋሙ የሚገኘውን ከፍተኛ ገንዘብም ማጣት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል።

በእርግጥ ኢትዮ ቴሌኮም የሚያቀርበው የቋሚና የተንቀሳቃሽ ስልኮችም ሆነ የዳታ (ኢንተርኔት መረጃ) አገልግሎት በጥራትም ሆነ በብዛት ቅርብና ሩቅ ካሉ ተመሣሣይ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ አናሳና ኋላ ቀር ነው። ነገር ግን ድርጅትን መሸጥ ጥራትን ለማሻሻል ብቸኛ መፍትሄ ተደርጎ መታየት የለበትም። መንግሥት ወደግል ይዞታ ያዛወራቸውን ከ230 በላይ ድርጅቶች ላይ የተደረገ ሰፋ ያለ ዳሰሳ የሚያመለክተውም ይህንኑ ወደግል መዛወር ለአትራፊነት እና ለአገልግሎት መሻሻል ዋስትና አለመሆኑን ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እጅግ ውድድር በበዛበት የዓለመ ገበያ አሸናፊ ሆኖ የወጣበት ልምድና የአሠራር ሂደት እንዲሁም በመንግሥት እና በአየር መንገዱ መሀከል ያለዉን ግንኙነት ሞዴል ከተደረገ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ ድርጅቶች ሁሉ ተወዳዳሪ አይሆንም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደማይቻል ተጨማሪ ማሳያ ነው።

ከኮቪድ-19 ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ አገራት አንዳንድ መሰረታዊ ቁሳቁሶችን በተለይም የህክምና መሣሪያዎች ከዚህ በፊት በሚያገኙት ፍጥነት እና ፎላጎት ልክ ማግኘት አቅቷቸው ተስተውለዋል። ይህም አገራት እርስ በርስ ያላቸውን የኢኮኖሚ ግንኙነት እና ጥገኝነት ቆም ብለው እንዲያስተውሉ ብሎም የአገራቸውን ሉዓላዊነት እናም የምርት ነፃነት ላይ በትኩረት እንዲሠሩ የማንቂያ ደውል ሆኖላቸዋል።

ከኮረና በኋላ የሚመጣው ጊዜ በኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲሁም በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዬች አገራችን የራሷን ጥቅም የምታስጠብቅባቸው መንገዶችን በግልፅ አሁን ላይ ሆነን መገመት ባይቻልም የኢኮኖሚ ሚዛኑን ለማስተካከል ግን መወሰድ ያለበት ጊዜ ተወስዶ በከፍተኛ ትኩረት እና ርብርብ አቅጣጫዎችን መለየት ያስፈልጋል። ዓለም ወደምን ዓይነት ኢኮኖሚዊ ሥርዓት እያመራች እንደሆነ መገመት በሚያዳግትበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ከትርፉ ጉዳቱ ያመዝናል። የሚወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች አሁን ካለንበት ችግር የሚያወጡን ብቻ ሳይሆኑ የወደፊቱንም ትውልድ የምጣኔ ሀብት እና የማኅበራዊ ነፃነቱን በምንም ዓይነት መልኩ አደጋ ላይ የማይጥሉ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት።

ከዚሁ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የቴለኮም የአከሰዮን ድርሻ ዋጋ ዓለም ላይ በእጅጉ ወርዷል። በሁሉም የገበያ መረጃ ቋቶች ላይ ማየት እንደሚቻለው ወደ 40 ገደማ የሚሆኑ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የቴሌ ካምፓኒዎች የአከሰዮን ደርሻ ዋጋቸዉ ቀይ ዞን ውስጥ ገብቷል። በዚህ ወቅት የሚደረግ ፕራይቬታይዜሽን የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ መጠን የቱንም ያህል ቢሆን ገዥ ያጣ ንብረት በሚጣልበት ዋጋ እንደተሸጠ ይታሰባል።

እንደአገር በዚህ ወቅት የምንወስናቸው ውሳኔዎች ምን እንዲያመጡልን እንፈልጋለን የሚለውን በሰከነ መንፈስ ማየት ካልተቻለ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አንድንም። ወቅቱን እንደምናየው የዓለም አሰተሳሰብን እየፈተነ ነው፤ እስካሁን በሄድንበት መልኩ አዲስ መንገድ ልንጀምር ይቅርና እስካሁን የሄድንባቸውን መንገዶችም ቆም ብለን ማየት ያለብን መሆኑን ያሳመነ ጊዜ ላይ ነን። መላው ዓለም ይህን በሚያሰላስልበት ወቅት አገራችን ኢትዮጵያን ያስተዋልን እንደሆነ ደግሞ እጅግ ከባድ በሆነ በድርብብ ጫና ውስጥ እንዳለች ለመረዳት አዳጋች አይደለም። የኮቪድ ወረርሽኝ አዳጋ ኢኮኖሚያችን ላይ እያመጣ ያለውንና በቀጣይነት የሚያመጣው ጫና በቅጡ ባለየንበት፣ እንደአገር ተረጋግትን ወደፊት ለመጓዝ በምን መልኩ እንሂድ የሚለው ባልጠራበት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የመገንባት ሂደቱ ፈቅ ባላለበት፣ የአንዱ ኃይል የተደላደለ የሚለው የመፍትሄ መንገድ ለሌላው ኃይል ገደል እንደሆነ በሚታሰብበት ከሁሉም የባሰው ደግሞ ለመስማማትም ሆነ ላለመስማማት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያያት እና መደራደር እንደተራራ በገዘፈበት በዚህ ውዥንብርና ምስቅልቅል ሰዓት የትኛውንም ዘላቂ ተፅእኖ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ህዝብን ሳያማክሩ፤ እንደአገር የሚመለከታቸውን አካላት ሳያሳትፉ ብሎም ሕጋዊ ቅቡልነትን ሳያረጋግጡ ይህን ዓይነት ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት መንደርደር እንደአገር ያሉብንን ችግሮች ከማግዘፍ እና ከማወሳሰብ የዘለለ ሚና ይኖረዋል ብሎ ለማመን ይከብዳል።

በተጨማሪም ሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ከገባው ቃል በተቃራኒ ያለበቂ ውይይት እና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ እሄደበት ያለው ጥድፊያ ከዚህ ቀደም በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እየተመከሩ የምጣኔ ሀብት ሪፎርም ያካሄዱ እና በዚያ ምክንያት የተቋሞቹ የረጅም ጊዜ ጥገኛ የሆኑ አገራትን ከሄዱበት መንገድ ጋር ተመሣሣይ ነው። አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ይህን መሰል በጣም ዘላቂ እና የወደፊት የአገራችን እጣ ፈንታ ላይ ትልቅ ውጤት ያላቸው እንዲሁም ወደፊት ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት እንኳን ሊያስተካክላቸው የማይችሉ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ መብት በፍፁም የለውም። በአጠቃላይ ገዢው ፓርቲ ለአገር ይጠቅማል ብሎ የሚያስባቸውን እና እንደዚህ ዓይነት የረጅም ጊዜ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ጉዳዮች እንደሚተገብር በምርጫ ወቅት ከሚወዳደርበት የፖሊሲ ሰነዶች መካከል አድርጎ የሕዝብን ፈቃድ ካገኘ ፖሊሲዎችን መተግበሪያ ሁላችንም የምናገኘው ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል።

በመሆኑም ገዢው ፓርቲ ይህን በአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ስትራቴጂክ ሴክተር ላይ ሕጋዊ ቅቡልንትን ሳያረጋግጥ፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ቅድሚያ ሳይሰጣቸው፤ በቂ ጥናት ሳይደረግ እና የንብረቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብና ወኪሎቹ ሳይመካከሩ ከየትኛውም ኃይል ይሁንታን ሳይጠብቅ በውጭ ጫና እና ማባበያ የወሰነውን ውሳኔ በመቀልበስ የኢቲዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ እየሄደበት ያለውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም እናሳስባለን።

 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!