Lidetu Ayalew

አቶ ልደቱ አያሌው

ሕገ መንግሥት በመጣስ የተፈጸመባቸውን በደል አመለከቱ
የዋስትናው ጉዳይ ቀርቶ የፍርድ ሒደቱ ይቀጥል ብለዋል

ኢዛ (ረቡዕ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 21, 2020)፦ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ የሰጠው ትእዛዝ ሊፈጸምላቸው ያልቻሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ የዋስትና ጥያቄው ቀርቶ የተከሰሱበት የፍርድ ሒደት እንዲቀጥል መጠየቃጠቸው ተሰማ። አቶ ልደቱ ይህንን ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ነው።

ሕገ መንግሥቱን በጣሰ መልኩ የፍርድ ቤት ውሳኔን ሳያስፈጽሙ የቀሩትን አካላት “በአማተሮች የሚሠራ ቴአትር” በማለት ድርጊቱን የተቹትና የኮነኑት አቶ ልደቱ፤ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ባለመፈጸም ጊዜ እየባከነ በመኾኑ፤ የዋስትና ጥያቄውን ትተው የፍርድ ሒደቱ ይቀጥል የሚል አቋም እንዲይዙ እንዳስገደዳቸው ተጠቁሟል።

ፍርድ ቤቱ በሕገወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ በመያዝ በተከሰሱበት ወንጀል በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የተሰጠው ትእዛዝና ከትናንት በስቲያም አቶ ልደቱን አስሮ የያዘው የቢሾፍቱ ፖሊስ ከማስጠንቀቂያ ጋር ያስተላለፈው ትእዛዝ ሊፈጸም አልቻለም።

የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የማይፈጸም ከኾነ ፍርድ ቤቱ በፖሊስ አዛዡ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ትእዛዝ ሰጥቶም እስካሁን ትእዛዙ ተፈጻሚ አልኾነም።

አቶ ልደቱ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሏቸው ፖሊስ ሕገ መንግሥቱን ጥሶ የእርሳቸውንም መብት ጥሶ እርሳቸውን ማሰሩ ሕገወጥ ተግባር ስለመኾኑ በመጠቆም ፍርድ ቤቱ ያደረገውንም ጥረት አድንቀዋል። ከዚህ በኋላ ግን ከዚህ በላይ አልጠብቅም የፍርድ ሒደት ይቀጥል ብለዋል።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ አቶ ልደቱ ለፍርድ ቤቱ የገለጹት ሌላው ነጥብ፤ ፖሊሶች በተከሰሱበት በአንደኛው የክስ መዝገብ እንደተፈቱና የታሰሩት በሌላው መዝገብ መኾኑን እንደገለጹላቸውና እርሳቸው ግን ለሰከንድም ያልተፈቱ መኾኑን ነው።

በዛሬው ችሎት የቢሾፍቱ ፖሊስ ተወካይ ያልቀረቡ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮምሽን ተወካይ መገኘታቸው ታውቋል። ፍርድ ቤቱም የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አቶ ልደቱ ፈትቻቸዋለሁ ያለበትን የመዝገብ ማስረጃ እንዲያቀርብ ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ ይህንንም የመዝገብ መረጃ የቢሾፍቱ ፖሊስ በነገው ዕለት እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ