Lemma Megersa and Taye Dendea

አቶ ለማ መገርሳና አቶ ታዬ ደንድአ

አቶ ታዬ ደንደአ፤ አቶ ለማ ምንም ዐይነት ተቃውሞም ኾነ የተለየ ሐሳብ አቅርበው እንደማያውቁ ተናገሩ

ኢዛ (እሁድ ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 1, 2019)፦ አሁን ላለው ለውጥ ቀዳሚ ሚና እንዳላቸው የሚታወቁት የመከላከያ ሚኒስትሩና የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፣ የመደመር ፍልስፍናንና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶቹን ውሕደት ያልደገፉት መኾኑን ገልጸዋል።

አቶ ለማ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የኦሮምኛ ፕሮግራም በሠጡት ቃለምልልስ፣ በመደመር ፍልስፍና ላይ ያላቸውን ልዩነት ሲገልጹ እንደነበር አስታውቀው፤ ይኽም ሁላችንም ሊገባን ይገባ ነበር ብለዋል። እኔም አልገባኝም በማለትም ከመደመር ፍልስፍና ተቃርነዋል።

በተለይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ለማዋሐድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደማይደግፉት ያመለከቱት አቶ ለማ፤ ለዚህ ልዩነታቸው ከጠቀሱዋቸው ምክንያቶች አንዱ የኦሮሞ ሕዝብ ላቀረበልን ታላላቅ ጥያቄዎች ቀድሞ መልስ መሥጠት ስለሚያስፈልግ ነው የሚል ነው።

ይህንንም ሲያብራሩም፤ “እኛ የኦሮሞ አመራር አባላት የኦሮሞ ሕዝብ አምኖ ያቀረበልን ትላልቅ ጥያቄዎች ስላሉ፣ ለነሱ መጀመሪያ መልስ መሠጠት አለበት በሚል ነው።” ብለዋል።

“እነዚህን ጥያቄዎች እንመልስላችኋለን ብለን ቃል ገብተናል። ሕዝባችን ይህንን ጥያቄ ያቀረበልን የትናንቱን ኦሕዴድ ስም ለውጠንለት፣ ስሙን ለውጠን ኦዴፓ ካልን በኋላ ነው። ስለዚህ ሕዝቡ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ … ብሎ የሠጠው ለአገራዊ ፓርቲው ሳይኾን ለኦዴፓ ነው። ስለዚህ የሕዝቡን ጥያቄ ሳንመልስ፤ ይህንን ማድረግ ትክክል አይደለም። እምነት ማጉደል ይኾናል። እናም ጥያቄዎቹን ቆጥሮ እንደሠጠን - መመለስ። በጥቅል ሲታይ ግደሞ፤ ውሕደቱ ጊዜው ካለመኾኑም በላይ በችኮላ የሚታይበትና ጥርጣሬ የሚያጭር ስለመኾኑም በዚሁ ቃለምልልሳቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላስ ምን ያደርጋሉ የሚል አንደምታ ላለው ጥያቄም አቶ ለማ፤ “ከዚህ በኋላ ከድርጅቱ ውጣልን ብለው እስካልውሰኑ ድረስ፤ ልዩኔቴን ይዤ እሟገታለሁ። እኔ ባቻ ሳልኾን ቅራኔ ያላቸው የሚከራከሩ ብዙ አሉ። ከኾነልን እናስተካክላለን። ካልኾነ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ተመካክረን የመበጀውን እናደርጋለን።” በማለት ምላሽ ሠጥተዋ።

በአቶ ለማ የተቃርኖ ጉዳይ ላይ የአቶ ታዬ ደንድአ ምላሽ

ይኽንኑ የአቶ ለማን ተቃርኖ አስመልክቶ ቃለምልልስ ያደረጉት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የኦሮሚያ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የኾኑት አቶ ታዬ ደንድአ፤ በመደመር እሳቤው ላይና በውሕደቱ ላይ በየደረጃው የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ “መጀመሪያ በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ በተደረገው ስብሰባ በሙሉ ድምፅ ተስማምተው ነው ያጸደቁት። እኛ ምንም ዐይነት የልዩነት ሐሳብ አልሰማንም” ብለዋል።

አክለውም፤ “እኛ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስንገናኝ፣ በስብሰባው ላይ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሐሳቦች ተነስተዋል። ግልጽነትና ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሐሳቦች ተነስተዋል። አንደኛ በፌዴራሊዝሙ ላይ ይሔ የፓርቲዎች ውሕደት ራስን በራን ከማስተዳደር አንጻር፤ አሁን ተዘርግቶ ካለው የፌዴራሊዝም መዋቅር አንጻር ሊያመጣ የሚችለው ተጽዕኖ ምን ሊኾን እንደሚችል ያነሱ የውጭ ተሳታፊዎች አሉ። በዚያ ላይ ግልጽ የኾነ ማብራሪያ ተሠጥቷል። እናም የውሕደቱን አስፈላጊነት ማዕከላዊ ኮሚቴው በሙሉ ድምፅ ነው ያጸደቀው። በዚያ ጉዳይ ላይ ግልጽ እንዲኾኑ የተፈለጉ ጉዳዮች ከመነሳት ውጭ፤ የተለያ አቋም ያንጸባረቀ፣ ያራመደም አልነበረም። እሳቸውም (አቶ ለማ) መድረኩም ላይ ነበሩ፤ በዚያ ጉዳይ ላይ የተለየ ሐሳብ እንዳላቸው፤ ውሕደቱ አስፈላጊ አይደለም፤ እሳቤውም አያስኬድም የሚል ሐሳብ አላመጡም። የተለየም ደግሞ ሌላ አማራጭም ሐሳብ አለ፤ ማየት ያለብን የሚል አልቀረበም።” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የማዕካላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ በውጭ ልዩነት አለ ተብሎ የሚወራውን ነገር አስመልክቶ የስብሰባው ተሳታፊዎች “ልዩነት አለ ወይ?” በማለት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ጠቅሰው፤ “ምንም ልዩነት የለንም። በመደመርም፣ በውሕደቱም አብረን እየሠራን ነው። ምንም ችግር የለም ብለዋል ሁለቱም። እኛ እስከምናውቀው ድረስ የተለየ አቋምና ሐሳብ ያራመደ አልነበረም” ያሉት አቶ ታዬ፤ አቶ ለማም ምንም ዐይነት ተቃውሞም ኾነ የተለየ ሐሳብ አለማቅረባቸውን ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!