ደኢሕዴን ብልጽግና ፓርቲን ተቀላቀለ

ለብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶች ውሳኔ
በብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ ላይ ሕወሓት እስካሁን በኦፊሴል ውሳኔዋን አላሳወቀችም
ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 28, 2019)፦ ከሕወሓት በስተቀር ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና አምስቱ አጋር ድርጅቶች በሙሉ የብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል ውሳኔ አሳልፈዋል። ሕወሓት ግን እስካሁን በኦፊሴል ውሳኔዋን አላሳወቀችም፤ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ግን ውሳኔውን የሚወስነው የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔው ነው ተደምጠዋል።
ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ አስቸኳይ ጉባዔ በመጥራት የብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል ቀድመው ውሳኔ በማሳለፍ አቋማቸውን ያሳወቁት አጋር ድርጅቶች ሲሆኑ፣ ትናንትናና ዛሬ ደግሞ ኦዲፓ፣ አዴፓና ደኢሕዴን ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ይህም ውሳኔያቸው፤ ከሕወሓት ውጭ የኢሕአዴግ አባል ድርጀቶችና አጋር ድርጅቶች በሚል የሚታወቁት ሁሉም የብልጽግና ፓርቲን በመቀላቀል፣ ፓርቲውን ለመመሥረትና በአዲሱ ፓርቲ ፕሮግራም ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ውሳኔ ማሳለፋቸውን የሚያረጋግጥ ኾኖ ተገኝቷል።
የብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል ዛሬ ውሳኔውን ያሳለፈው ደኢሕዴን፤ የብልጽግና ፓርቲው አካል ለመኾን የሚያበቃውን ውሳኔ የወሰነው በሙሉ ድምፅ ነው።
ሕወሓት የዚህ ፓርቲ አካል ለመኾን የማይሻ መኾኑን በይፋ ያልገለጸ ሲሆን፣ ቀጣይ እርምጃው ምን ሊሆን እንደሚችል እየተጠበቀ ነው። ኾኖም በጉዳዩ ላይ ለመነጋገርና ውሳኔ ለማሳለፍ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራቱ ታውቋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ላይ ግን፤ በተለይ የሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባለፈው ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ከሠጡት መግለጭ፣ እንዲሁም የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ ቀርበው ከሠጧቸው ቃለምልልሶች ለመረዳት የሚቻለው አንደምታ፤ ሕወሓት በውሕደቱ አካሔድ ላይ ያለውን ተቃውሞ አጉልተው የሚያሳዩ ኾነው ተገኝተዋል። (ኢዛ)