ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ተወሰነ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
በተከሰቱ ጥፋቶች እጃቸው ያለበት አካላትን ለሕግ የማቅረብ ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል
ኢዛ (ሰኞ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 9, 2019)፦ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መንግሥት ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገለጸ።
ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ በኾነው መረጃ መሠረት፤ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎችን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለመከላከል ነው።
ከፌዴራል ፖሊስ ጥበቃው ባሻገር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሲዎች በደኅንነት ካሜራዎች እንዲታገዙ ይደረጋል ተብሏል። በበር ላይም ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እንዲካሔድ በዚሁ ውሳኔ ላይ ስለመተላለፉ ይኸው መረጃ ያመለክታል።
በመረጃው ማጠቃለያ ላይም፤ “በተከሰቱ ጥፋቶች እጃቸው ያለበት አካላትን ለሕግ የማቅረብ ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ይላል።
በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 37 መኾናቸው ይታወቃል። (ኢዛ)



