ባልደራስ እስክንድር ነጋ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዓርማ (በግራ)፣ እንዲሁም የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ

ለደረሰው እልቂትና ንብረት ውድመት የአንድ ቀን ጀንበር የወለደው ችግር አይደለም

ኢዛ (ሐሙስ ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. July 9, 2020)፦ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ እና አመራሮችን መታሰር ተከትሎ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፤ ሰሞኑን ጽንፈኞች በቀሰቀሱት አመጽ ለደረሰው እልቂትና ንብረት ውድመት የአንድ ቀን ጀንበር የወለደው ችግር አለመኾኑን ገለጸ። ፓርቲው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገሪቱ እየታየ ለሚገኘው ሥርዓት አልበኝነትና ሲልም ሽብርተኛነት ቀጥተኛ ተጠያቂዎች እንደሆኑ አበክሮ እንደሚያምን በመግለጫው አሳውቋል።

ባልደራስ “ለሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ያለን ታማኝነት በሐሰት ውንጀላ አይገታም” በሚል ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤ በማንም ዜጋ ላይ የሚደረግ ግድያን በፍጹም እንደሚያወግዝ ገልጾ፤ በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈፀመውንም ግድያ እንደሚያወግዝ እና ገዳዮቹንም በፍትሕ እንዲዳኙ አበክሮ ጠይቋል።

ባልደራስ የአዲስ አበባን ሕዝብ ለፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደራጅ መቆየቱንና አሁንም በዚሁ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ሕዝብን ማደራጀት እንደሚቀጥል አስታውቋል። ፓርቲው የቆመለትና የተቋቋመበት ዓላማም ይህ ነው ብሏል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የዘፋኝ ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ለደረሰው የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂው መንግሥት መኾኑን በመግለጽ፤ የሚከተሉትን ባለሦስት ነጥብ ጥያቄዎችን አቅርቧል።

1ኛ/ መንግሥት ለጠፋው የንጹሐን ዜጎች ሕይወት፣ ለንብረታቸው መውደም፣ ስደት፣ የሥነ ልቦና ቀውስና የኢኮኖሚ ድቀት ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ካሳ በመክፈል፣ የተሰደዱ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ሕይወት እንዲጀምሩ አስፈላጊውን ሁሉ በአስቸኳይ እንዲያደርግና እንዲሁም አስተማማኝ ጸጥታና ሰላም የማስፈን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እንጠይቃን።

2ኛ/ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ምክር ቤት በሚል ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉትና በቴሌቭዥን በተላለፈ ውይይት ላይ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሚኒስቴርና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር የሰጡት አስተያየት የተጠርጣሪዎችን በፍርድ ፊት ንጹሕ ኾኖ የመታየት ሰብአዊ መብታቸውን የጣሰ ከመኾኑም በላይ፤ እንደቀድሞው ከፍትሕ በፊት ዜጎችንና ድርጅቶችን የማሸማቀቅና የዳኞችን ነፃነት በእጅጉ የሚጋፉ ኾኖ አግኝተነዋል። በመኾኑም በዕለቱና ከዚያ ተከትሎ የተከሰቱት ጉዳዮችን የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ አካል ተቋቁሞ የደረሰውን መጠነ ሰፊ ውድመት እንዲመረመር አበክረን እንጠይቃለን።

3ኛ/ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተከሰተው የንብረት መውደም የጸጥታ አካል ምንም ዐይነት ምላሽ ሳይሰጥ ቆሞ ተመልካች እንደነበረ የከተማው ነዋሪ የሚያውቀው ሐቅ ነው። እንደ ባልደራስ እምነት ይህ ፍጹም ተገቢ ያልኾነ ቸልተኛነትና እሱን ተከትሎ የመጣ የማኅበረሰቡ እራሴን ከሽብርተኛ ጥቃት ልከላከል ብሎ መነሳት ፍጹም ተፈጥሯዊ ግዴታ በመኾኑ የሚደገፍ ነው። በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ፖሊሶችና የጸጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ በከተማ ውስጥ የተከሰተውን ኹከት በሚመለከት የከተማውን ጸጥታ በማስከበር ረገድ በተደጋጋሚ ቸልተኛነት ማሳየታቸውን ነዋሪው ሕዝብ በትዝብት ተመልክቶታል። ይህም የኾነበት ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ በፖሊስነት እየተመለመሉና እየሰለጠኑ ያሉት የከተማው ነዋሪ ሥነ ልቦና የሌላቸውና ከሌላ አካባቢ የመጡ በመኾናቸው እንደኾነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል። ይህ ሁኔታ መለወጥ እንደሚኖርበትና የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ከነዋሪዎቿ በተውጣጣ የፖሊስ ኃይል መጠበቅ እንዳለበት ፓርቲያችን በጽናት ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።”

ባልደራስ በዚሁ መግለጫው፤ የፓርቲው መሪ አቶ እስክንድር ነጋና አብረውት የታሰሩት ጓዶቹ በሐሰት ተወንጅለው ሲታሰሩ ይህ የመጀመሪያቸው አለመኾኑን ገልጾ፤ እስክንድር በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን በኢትዮጵያ ሐቀኛ ዴሞክራሲና ለእውነተኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ ሲታገል በሐሰት ተወንጅሎ ከ10 ዓመት በላይ መታሰሩን አስታውሷ። አሁንም የቀጠለው ይኸው የቀድሞ በሐሰት ወንጅሎ የማሰር አባዜ መኾኑን ጠቅሶ፤ “ይህ እውነታ የሚያመለክተው ገዢው ፓርቲ ለራሱ ብልጽግና የተሰኘ የዳቦ ስም ቢሰጥም፣ በተግባር ከብልጽግና ይልቅ ኢሕአዴግ ቁጥር ሁለት ኾኖ መቀጠሉን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው” በማለት ተችቷል።

በመግለጫው ማጠቃለያም፤ “ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በተከሰተው ግጭት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ መጽናናትን፣ አካላቸው ለተጎዳ ቶሎ ማገገምን እየተመኘ፣ ንብረታችው ለጠፋ ካሳ እንዲሰጣቸው ያሳስባል።” ብሏል። የባልደራስን ሙሉ መግለጫ አስነብበኝ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ