AEUP support in North AmericaEthiopia Zare (ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2004 ዓ.ም. September 23, 2011)፦ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ “ከሽብርተኞች ጋር ንክኪ አላቸው” የሚል መሰረተ ቢስ ክስ እየመሰረተ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አባላትን፣ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችንና አርቲስቶችን ወደ እስር ማጎሩን አስመልክቶ በሰሜን አሜሪካ የመኢአድ ድጋፍ ሰጪ ማኅበር ትናንት ባወጣው መግለጫ እስረኞቹ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።

 

መግለጫው በቅርቡ የታሰሩትን ጨምሮ በየክፍለ ሀገሩ የታሰሩ የፖለቲካ አስረኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከመጠየቁም በላይ፤ ለዚህም መሠረተ ቢስ ክስና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደረግ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ጠ/ሚ መለስና ግብረ አበሮቻቸው ተጠያቂ መሆናቸውን በጥብቅ እናስታውቃለን ብሏል።

 

ይኸው መግለጫ፤ “… የኢትዮጵያ ሕዝብ እየደረሰበት ስላለው መራራ የኑሮ ሁኔታና ለዚህም መፍትሄ የሚላቸውን ሀሳቦች በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ ወጥቶ ለመግለጽ የጠየቀው ጥያቄ እገዳው ተነስቶ ብሶቱን መግለጽ እንዳለበት እናምናለን። ሰልፍ የማድረግ መሠረታዊ መብቱ ስለሆነም ከማንም ፈቃድ አያስፈልገውም እንላለን፤ በነቂስ በአደባባይ ወጥቶም ብሶቱንና ፍላጎቱን መግለጹን የምንደግፍ መሆኑን እንገልጻለን። ይህ መብቱ እስኪረጋገጥለት ድረስ በሚቻለን አቅም ባገኘነው መድረክ ሁሉ ካለማሰለስ የምንታገል መሆኑን እንገልጻለን። …” በማለት ያለውን ቋም ይገልፃል።

 

በሰሜን አሜሪካ የመኢአድ ድጋፍ ማኅበር መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ.ም. “የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርና ግብረ አበሮቹ በተቃዋሚዎች ላይ በሚያካሂዱት የእሥር ዘመቻ” በሚል ርዕስ ያወጣውን ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ይነበባል።

 

የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርና ግብረ አበሮቹ በተቃዋሚዎች ላይ በሚያካሂዱት የእሥር ዘመቻ

ከሰሜን አሜሪካ የመኢአድ ድጋፍ ማኅበር የተሰጠ መግለጫ

(መስከረም 11፤ 2004 ዓ.ም.)

የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርና ግብረአበሮቹ በተከታታይ በተቀዋሚ ድርጅቶች አመራርና አባላት፤ በግል ጋዜጠኞችና አርቲስቶች ላይ ባጠቃላይ በተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት ላይ እያካሄዱ ያለውን የማሰርና የአፈና ዘመቻ በጥብቅ እናወግዛለን። በቅርቡም ያለአንዳች ማስረጃ በፍርሃት ላይ በተመሠረተ ስሌት ብቻ የግል ኑሮአቸውን በሰላም ከሚያከናውኑበት ቦታ በሽብርተኝነት በመወንጀል በግፍ ያሰሯቸውን፤

 

1. አቶ ደበበ እሽቱ፤ አርቲስት፤

2. አቶ አንዱአለም አራጌ፤ የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ም/ፕሬዘደንትና የሕዝብ ግኑኝነት ሃላፊ፤

3. አቶ በቀለ ገርባ፤ የተቃዋሚ ድርጅት ሥራ አመራር አባል

4. አቶ ኦልባና ሌሊሳ፤ የተቃዋሚ ድርጅት ሥራ አመራር አባል

5. አቶ ናትናኤል መኮንን፤ የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ አባል

6. አቶ ዘመኑ ሞላ፤ የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ አባል

7. አቶ እስክንድር ነጋ፤ ጋዜጠኛ

8. ወ/ት ርዕዮት ዓለሙ፤ ጋዜጠኛ

9. አቶ ውብሸት ታዬ፤ ጋዜጠኛ

10. አቶ ስለሺ ሃጎስ፤ ጋዜጠኛ

ሌሎችም እንደዚሁ በሥር ላይ የሚገኙ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ እንዲለቅ በጥብቅ እናሳስባለን። እነዚህን ግለስቦች የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና የዓለም ሕብረተስብም ጭምር በተለይም የዓለም አቀፍ ስብአዊ መብት አስጠባቂ ድርጅቶችና የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ደህንነት ማኅበር ለሀገሪቱ ደህንነት ተቆርቁረው በነፃ ሃሳባቸውን ከመግለጽ ሌላ በሽብርተኝነት የሚያስከስስ ወንጀል እንደሌለ ባወጡአቸው መግለጫዎች አስታውቀዋል። የዘረኛው አምባገነን መንግሥት ዓይን ባወጣ መልኩ ፈጥሮ ያቀረበው ክስ የሚያስገርም ከመሆኑም በላይ በዓለም ሕዝብ እይታም አሳፋሪ ተግባር ነው። ዋነኛ ዓላማው ግን በተቃዋሚ ድርጅቶች፤ አባላትና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሮ ብሶቱን እንዳይገልጽና ለዘረኛና አምባገነን አገዛዙ እንዲንበረከክ ለማድረግ እንደሆነ አያጠራጥርም።

 

በመሠረቱ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር በመሣሪያ ሀይል በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ የተጫነ ሲሆን እነሆ ላለፉት ሀያ ዓመታት እንደፈለግው ሲያስር፤ ሀገር ቆርሶ ሲሸጥ፤ ሕዝባችንን በረሀብ ሲቀጣ፤ ለዘመናት ተሳስረው የኖሩ ወገኖቻችንን በዘር ከፋፍሎ ለዘመናት የሚቆይ ውዝግብ ውስጥ ለመክተት ያላሰለስ ጥረት እያደረገ ፤ያለ ሀይሉን በመጠቀም የሕዝቡን የምርጫ ድምጽ በጉልበት በመንጠቅ በሥልጣን የቆየ ነው።

 

በትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የሚመራው አምባገነን መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች፤ የሚፈጥራቸው መ/ቤቶች የጦርና የፖሊስ ሀይሎችን ጨምሮ ሁሉም የአገዛዙን ደህንነት የሚጠብቁና ዕድሜውን የሚያራዝሙ ተግባሮች እንዲፈጽሙ ታቅደው የተፈጠሩና የተዋቀሩ መሆኑን ለአንድ አፍታም መዘንጋት የለብንም።

 

ስለሆነም በሰሜን አሜሪካ የመኢአድ ድጋፍ ማኅበር፤

1. ከፍ ብሎ ስማቸው የተጠቀሱትና ሌሎችም በየክፍለ ሀገሩ የታሰሩ የፓለቲካ እሥረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቀ ለዚህም መሠረተ ቢስ ክስና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደረግ የሰብዓዊ መብት ረገጣ መለስና ግብረ አበሮቹ ተጠያቂ መሆናቸውን በጥብቅ እናስታውቃለን።

 

2. የኢትዮጵያ ሕዝብ እየደረሰበት ስላለው መራራ የኑሮ ሁኔታና ለዚህም መፍትሄ የሚላቸውን ሀሳቦች በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ ወጥቶ ለመግለጽ የጠየቀው ጥያቄ እገዳው ተነስቶ ብሶቱን መግለጽ እንዳለበት እናምናለን። ሰልፍ የማድረግ መሠረታዊ መብቱ ስለሆነም ከማንም ፈቃድ አያስፈልገውም እንላለን፤ በነቂስ በአደባባይ ወጥቶም ብሶቱንና ፍላጎቱን መግለጹን የምንደግፍ መሆኑን እንገልጻለን። ይህ መብቱ እስኪረጋገጥለት ድረስ በሚቻለን አቅም ባገኘነው መድረክ ሁሉ ካለማሰለስ የምንታገል መሆኑን እንገልጻለን።

ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር!

በሰሜን አሜሪካ የመኢአድ ድጋፍ ሰጭ ማኅበር

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!