አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አቶ አገኘሁ ተሻገር (በግራ)፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ (በቀኝ)

“ትሕነግ እና ኦነግ ሸኔን በመተባበር መታገል ያስፈልጋል” አቶ ተሻገር አገኘሁ

ኢዛ (ረቡዕ ነኀሴ ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 12, 2020)፦ ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ተናገሩ በተባለው ጉዳይ ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባሉበት በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ እንዲገመገም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ ማሳለፉ ተገለጸ።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሁለት ቀናት ሲያካሒድ የነበረውን ኮንፈረንስ ካጠናቀቀ በኋላ ዛሬ ረቡዕ ነኀሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን በተሰጠ መግለጫ፤ የአቶ ሽመልስ ሰሞናዊ ንግግር ዙሪያ በኮንፈረንሱ ላይ ውይይት የተደረገበት መኾኑ ተገልጿል።

የኮንፈረንሱን መጠቃለል ተከትሎ የአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደተናገሩት የአቶ ሽመልስ ሰሞናዊ ንግግር የግላቸው መኾኑን ጠቅሰው፤ ኾኖም ይህ ንግግራቸው ግለሰቡ ባሉበት በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ እንዲገመገም ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት በማንም እንደማይበጠስ የገለጹት አቶ አገኘሁ፤ በየትኛውም መንገድ የማይወዛወዝ ወንድማማችነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ብለዋል።

ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘም፤ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ወንድማማች ሕዝብ መኾኑን ጠቅሰው፤ ሕወሓት ሁለቱን ሕዝቦች ሊነጥል አይችልም በማለት አክለዋል።

አያይዘውም የአማራን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለማጋጨትና ለመነጠል ይሠራሉ ያሉዋቸውን፤ ትሕነግ እና ኦነግ ሸኔን ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመተባበር መታገል የሚያስፈልግ ስለመኾኑም መስማማታቸውን አክለው ተናግረዋል። የፓርቲው የሁለት ቀናት ውሎና የደረሰባቸውን ስምምነቶችና ውሳኔዎችን፣ ሌሎች ጉዳዮችንም በተመለከተ አቶ አገኘሁ ተሻገር ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ