አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና አቶ ደመቀ መኮንን

አቶ ተመስገን ጥሩነህ (ግራ) እና አቶ ደመቀ መኮንን (ቀኝ)

አቶ ደመቀ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ደርበው ያዙ
የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተነስተዋል
ሌ/ጄኔራል አበባው ምክትል ኤታማዦር ሹም ኾነዋል
የደኅንነትና የፌዴራል ፖሊስ በአዲስ አበባ አመራሮች እንዲመሩ ተደርጓል

ኢዛ (እሁድ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 8, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ቁልፍ በሚባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሹም ሽር አካሔዱ።

ዛሬ እሁድ ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት አቶ ደመቀ መኮንን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኾነው ተሹመዋል።

እስካሁን የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩትን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ኾነው እንዲሠሩ ተሹመዋል። እስካሁን የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል አደም ኢብራሒም የተሰጣቸው ኃላፊነት የለም።

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መከላከያውን እንዲቀላቀሉ ከተደረጉት አራት ጄኔራሎች መካከል አንዱ የኾኑት ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ ደግሞ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ኾነዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመኾን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመዋል።

የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት መሠረት የቀደመውን የኃላፊነት ቦታዎችን እንዲለቁ ከተደረጉት ውስጥ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አንዱ ናቸው። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ኾነው እንደተሾሙ ታውቋል።

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ሹመት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ኾነው እንዲያገለግሉ መሾማቸውንም ያመላክታል። አዲሱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር በመኾን የተሾሙት አቶ ደምበላሽ ገብረሚካኤል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር በመኾን ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል።

እስከዛሬ ድረስ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው በአቶ ደምበላሽ የተተኩ በመኾኑ፤ አዲስ የተሰጣቸው ኃላፊነት ይኑር አይኑር የተገለጽ ነገር የለም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ