ከኢትዮጵያ ቴሌቪዠንና ራዲዮ ድርጅት የኮበለሉ የስፖርት ጋዜጠኞች ቁጥር ሰባት ደረሰ
Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም 10 ቀን 2002 ዓ.ም. September 20, 2009)፦ ብዙውን ጊዜ "ሙያዊ ነፃነትን በመጫን" ከሚታወቀው የኢትዮጵያ ቴሌቪዠንና ራዲዮ ድርጅት በተለያዩ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና በዘመድ የቅጥር ጫናዎች ምክንያት ሥራቸውን እየለቀቁ ወደ ግሉ የሥራ መስክ የሚሠማሩ የመንግሥት ጋዜጠኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሆኑ ታወቀ። ጥቂት የማይባሉትም ሀገር ለቀው መሰደዱን ምርጫቸው አድርገዋል።
በዚሁ መሠረት ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራዲዮ ድርጅት ከምርጫ 97 በኋላ ከሀገር እንደወጡ የቀሩ የስፖርት ጋዜጠኞች ቁጥር ብቻ ሰባት ደርሷል። የስፖርት ጋዜጠኞቹን ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ያደረጋቸው በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተገኝታ ለመዘገብ ወደ ጀርመን አምርታ የነበረችው ሒሩት ገብረ-አምላክ ነች። ሒሩት ለዘገባ ከሄደችበት ጀርመን እስከ መስከረም 8 ቀን 2002 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ወደ ሀገርዋ አልተመለሰችም።
ከእሷ በፊት ከአማርኛው የስፖርት ዝግጅት ክፍል ስዊዘርላንድ ተጉዛ የቀረችውን ሐናን እና ወደ ጀርመን አመርቶ በዛው የከተመውን ኢዘዲን ከድርን ጨምሮ ሦስት ጋዜጠኞች እንደወጡ ቀርተዋል። ከኦሮምኛ እና ከትግርኛው ቋንቋ የስፖርት ዝግጅት ክፍልም እንደዚሁ 3 ጋዜጠኞች መኮብለላቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ድርጅት ምንጮች ገልጸዋል።



