የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ውዝግብ ተቋጨ
አቡነ ሳሙኤል የልማትና ተራድዖ ኮሚሽን ሥልጣን ፀደቀላቸው
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 18 ቀን 2002 ዓ.ም. October 28, 2009)፦ አቡነ ሳሙኤል ዕጣ የወጣላቸው የልማትና ተራድኦ ኮሚሽን ተቋም ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ በመሆኑ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 18 ቀን 2002 ዓ.ም. የፀደቀላቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።
ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ በሌሎች የቅዱስ ሲኖዶስ ጳጳሳት ላይ በመንግሥት ሰዎች የታገዘ ተጽዕኖአቸውን በማሳረፍ ላይ ቢሆኑም፤ ቅዳሜ ጥቅምት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በአጠቃላይ ስምምነት ያበቃል የተባለለት የሲኖዶሱ ጉባዔ ለሰኞ ጥቅምት 16 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ሲሆን፤ ጉባዔው በአባ ጳውሎስ ዕምቢኝ ባይነት በዕለቱም ሳይቋጭ አድሯል።
የቤተክህነት ምንጮች ውዝግቡ እልባት ሊያገኝ ያልቻለው፤ “አቡነ ጳውሎስ የአባ ሳሙኤልን የሥራ ምደባ እኔ ባልኩት መሠረት ይፈጸም፤ የሲኖዶሱ አባላት አባ ሳሙኤል ዕጣ በወጣላቸው መሠረት የልማትና ተራድዖ ኮሚሽን ተቋም ኃላፊ ሆነው ይቀመጡ መባሉን አልቀበልም በማለታቸው ነበር። ይልቁንም አቡነ ጢሞቲዎስን ጨምሮ ሌሎች ጳጳሳትን በመዝለፍና በማንጓጠጣቸውም ምክንያት ነው” ብለዋል።
ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ አባ ሳሙኤልን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ አርቀው በመወርወር በእሳቸው አስተዳደር ዙሪያ ተነስቶ የነበረውን ጥያቄ በሙሉ ለማዳፈን የሚፈልጉ ሲሆን፤ ከእሳቸው በተቃራኒ ወገን የቆሙ የሲኖዶሱ አባቶች ደግሞ “የሥራ ምደባ በሲኖዶሱ ውሳኔና በተመደበው ፈቃድ ወይም በዕጣ መሆን ይገባዋል እንጂ፤ አባ ጳውሎስ በሚሰጡትና ሊታጠፍ አይገባውም እያሉ በአምባገነንነት በሚሞግቱበት ትዕዛዝ መሆን የለበትም” የሚለውን አቋም ይዘዋል።
ብዙኀኑ ጳጳሳት ከአባ ሳሙኤል ወገን ሆነው፤ “በአዲስ አባባና በአቅራቢያው ወይም በአሰበተፈሪ ይመደቡ፤ ይህም ካልሆነ በልማትና ተራድዖ ኮሚሽን ውስጥ እንዲሠሩ ይሁን” የሚል ሃሳብ አቅርበው ነበር። “ማንም ሊያስፈራራኝና ሊዝትብኝ አይችልም …” ያሉት አባ ጳውሎስ “ተፈፃሚ መሆን ያለበት የእኔ ሃሳብ ብቻ ነው” በሚለው አቋማቸው ጸንተው እንደነበር ታውቋል።
ከእነ አባ ሳሙኤል ጋር የተጣሉበትን በቤተሰብ የመሥራት ችግር ጥያቄ ለማለዘብ ዋንኛ ተቀናቃኛቸውን ወደ መቀሌ ለማዝመት፣ የአዲስ አበባንም ሀገረስብከት በ5 ቦታ ለመሸንሸን ያላቸውን ፍላጎት ከጥቅምት 11 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ በተደጋጋሚ አንፀባርቀዋል።
አቡነ ሳሙኤል በመግቢያ ንግግራቸው ብዙኀን አባቶችን በሚማርክ መልኩና ታላቅ አባት መሆናቸውን በሚያስመሰክር ሁኔታ፤ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ጉባዔውን ጥፋት አጥፍተው እንደሆነ ይቅርታ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ደንብ መሰረት የአባቶች ሹመት በዕጣ ሳይሆን በፈቃዳቸው በሲኖዶሱ ውሳኔ እንዲሆን ያዛል።



