በእነ ብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመስጠት ህዳር 4 ተቀጠረ

Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. November 5, 2009)፦ ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በተያያዘ “እነ ብርጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞ” በሚል መዝገብ ክስ ከመሰረተባቸው 46 ግለሰቦች ውስጥ ዓቃቤ ሕግ የስምንቱ ንብረት እንዲታገድለት ጠይቆ ፍርድ ቤቱ ፈቀደለት። ንብረታቸው የታገደባቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ኮሎኔል አለሁበል አማረ እና አቶ ያረጋል ይማሞ በሌሉበት ሲሆን፤ በእስር ከሚገኙት ውስጥ ደግሞ ብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞ፣ አቶ ፅጌ ኃብተማርያም (የአቶ አንዳርጋቸው አባትና የ80 ዓመቱ አዛውንት)፣ አቶ አሳምነው ፅጌ እና አቶ ጌቱ ወርቁ (የዶ/ር ብርሃኑ የቅርብ ዘመድ) ናቸው።

 

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት የተከሳሾቹ ንብረት ይታገድልኝ በሚል ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ከተመሰረተባቸው ክስ አንፃር ሊቀጡ ከሚችሉት ቅጣት አንዱ የንብረት መወረስ በመሆኑን በመጥቀስ፤ የተከሳሾቹ ንብረት “ወደ ሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍና ተከብሮ እንዲቆይ” በሚል የንብረት እገዳ ጥያቄውን ማቅረቡ ታውቋል። ፍርድ ቤቱም የንብረት እገዳውን ለዓቃቤ ሕግ ፈቅዶለታል።

 

ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ግንቦት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሰረተባቸው 46 ግለሰቦች ውስጥ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ የነበሩት 14 ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ መስጠቱን መዘገባችን አይዘነጋም።

 

የዓቃቤ ሕግን እና የቀሪዎቹን 32 ተከሳሽ ግለሰቦች የመከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ፍርድ ቤቱ ተመልክቶ የጨረሰ ሲሆን፤ በመጪው ህዳር 4 ቀን 2002 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን ከአዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ ያስረዳል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ