የወ/ት ብርቱካን ቀበሌ በ300 ፌደራሎች ይጠበቃል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ መጋቢት 18 ቀን 2002 ዓ.ም. March 27, 2010)፦ የፌደራሉ መንግሥት አድማ በታኝ የፖሊስ ኃይል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች ተደጋገሚና ያልተቋረጠ “የአድማ ብተና” ሥልጠናዎችን እያካሄደ ነው።

 

 

ሥልጠናዎችን ከሚያካሂድባቸው ሥፍራዎች አንዱ ጃንሜዳ ሲሆን፣ በቀድሞው ወረዳ 13 ቀበሌ 03 ጽ/ቤት (አንበሣ ግቢ በስተጀርባ) የሚወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ አድማ በታኝ ፖሊሶች ካለፈው ረቡዕ መጋቢት 8 ቀን ጀምሮ በጃንሜዳ ልምምዳቸውን ቀጥለዋል። ሠራተኞችንና ተማሪዎች ወደ መ/ቤታቸውና ወደ ትምህርት ማዕከላት በሚያመሩበት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓት ተኩል ያለውን ጊዜ ጠብቀው የድንጋይ መከላከያ ጋሻና ቆመጥ በማንገብ ከ6 ኪሎ ወደ ጃንሜዳ በህዝቡ መሃል የሚተላለፉት የአድማ በታኞቹ ኃይሎች፤ “በመንግሥት በኩል በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ከምርጫው በፊት ሥነ-ልቦናዊ ሽብር ይፈጥሩ ዘንድ የታሰበ መሆኑ ተጠቁሟል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት ልዩ ስሙ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚታወቀው እና ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተወልዳ ባደገችበት ሠፈር ውስጥ 300 የሚሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ሲቪል ለባሽ የደህንነት ሠራተኞች በቀድሞ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 11 ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ ማስቀመጡ ታውቋል።

 

ለዚህ በመንግሥት በኩል የተሰጠው ምላሽም “በምርጫ 97 ጊዜ የሽብር ተግባር ጎልቶ የታየባቸውን አካባቢዎች ቀድሞ ለመቆጣጠር ከሚኖር ቀና ፍላጎት ነው” የሚል ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በቀጨኔ፣ በመርካቶ እና በቂርቆስ የገበያ ሥፍራ አካባቢ የአቶ መለስ መንግሥት የአድማ በታኝ ኃይሎቹን በካምፕ ከማስቀመጡም በላይ በኮተቤም ተመሳሳይ ሁኔታ መኖሩን ምንጮች ጠቁመዋል።

 

ጠ/ሚ መለስ በተወካዮች ምክር ቤት ሕገ-ወጦችን ከምርጫ በኋላ እንደሚከሱ በይፋ ከገለጹ በኋላ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች በጠቅላይ ሚንስትሩ ማስፈራሪያ ሳይበገሩና የሚመጣባቸውን ማናቸውንም ጥቃት በፀጋ በመቀበል ትግላቸውን ከመግፋትና ለኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት መከበር ከሚያደርጉት የሠላማዊ ትግል ወደኋላ እንደማያፈገፍጉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ህዝብ ማግኘት የሚገባውን የፍትህ የበላይነት እስከሚያገኝ በሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች በቁርጠኝነት መነሳት እንዳስደሰታቸውና በማስፈራራቱም ሆነ በአድማ በታኝ እንቅስቃሴ ህዝቡ ሳይታወክ የሚደግፈውን ፓርቲ ለመምረጥ ቆርጦ መነሳት እንዳለበት አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አክለውም፤ “የሚደረጉትን ጫናዎችንና አፈናዎችን በመቋቋም ከ150 በላይ ተመራጮችን በፓርላማ ማስባት ከተቻለና ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ ጥረት ከተደረገ፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት አጭር መንገድን ይፈጥራል” ብለዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!