Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 1 ቀን 2002 ዓ.ም. April 9, 2010)፦ መድረክ “በመንግሥትና በመንግሥቱ መገናኛ ብዙኀን የሚሰራጩ ገደብ የለሽ ስድቦች፣ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች፤ ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆኑና የሥነ ምግባር ደንቡን የሚፃረሩ በመሆናቸው በአስቸኳይ ይቁሙልኝ” ሲል መግለጫ አወጣ። በዕጩዎቼና በአባላቶቼ ላይ ደረሰ ያለውን አሰቃቂ ድርጊቶች ይፋ አድርጓል።

 

ሚያዝያ 1 ቀን 2002 ዓ.ም. ይፋ ባወጣው መግለጫ፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አንድ ላይ በመሆን መጭውን ምርጫ እናሸንፋለን የሚለው መድረክ፤ “ኢህአዲግን አይመርጡም ተብሎ በተገመቱ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት ለሌሎች እንደመቀጣጫ ሆኖ የተዘጋጀ ነው” ሲል የገዢውን ፓርቲ ተግባር ኮንኗል።

 

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በምረጡኝ ቅስቀሳ የሚነገሩ መረጃ የሌላቸውና ሕገ-ወጥ የሚባሉ አባባሎች ከምርጫ በኋላ የሚያስከስሱና የሚያስጠይቁ ይሆናሉ በማለታቸው ስጋታችን እጥፍ ድርብ ሆኖ በውስጣችን አለመረጋጋት ፈጥሮአል። ከዚህም ሌላ በተለያዩ ክልሎች በአባሎቻችን ላይ ድብደባ፣ ዛቻና የማስፈራራት ተግባራት እየተፈጸሙ ይገኛሉ” በማለትም አክሏል በመግለጫው።

 

“በምንንቀሳቀስበት ሥፍራ ሁሉ የክርስትና ስም እያወጣልን ነው። ’በኢህአዲግ ዘራሽ’ ሚዲያዎች ስማችን ጥላሸት ሲቀባ ውሎ እያደረ ነው …” የሚለው መድረክ፤ “የመከላከያ ኃይላችንን የመተንኮስ ተግባር ፈጽማችኋል …” የሚል ክስና አሉባልታ እየተነዛ መሆኑንና ይህም ለሀገሪቱ ፖለቲካ ጤናማ አለመሆኑን ገልጿል።

 

የመከላከያ ኃይላችንን የመተንኮስ ተግባር ፈጽማችኋል ብንባልም፤ እኛ ግን የሀገራችንን ዳር ድንበር በመጠበቅ ላይ የሚገኘው ሠራዊት የራሳችን ወገን ስብስብ መሆኑን የምናምንና ዜግነታዊ ኃላፊነት የሚሰማቸው የፖለቲካ ኃይሎች ነን ያለው መድረክ፤ በጥምረቱ አባላት፣ ዕጩዎችና ደጋፊዎች ላይ ይፈጸማል ያላቸውን ችግሮች በመግለጫው እንደሚከተለው ዘርዝሯል።

 

1ኛ. በአንዳንድ ከተሞች የመድረከን እንቅስቃሴ ለመግታት ሰዓት እላፊ እስከማወጅ ተደርሷል።

2ኛ. በሃድያ ዱና ወረዳ ውስጥ ድብደባ የደረሰባቸው አባሎቻችን አቶ ተስፋዬ ቡቂ - የክልል ዕጩ፤ አቶ ዳዊት ለገሰ፣ አቶ አየለ ቡፌቦ ሲሆኑ፤ እነዚህ ዕጩዎች እጅና እግራቸው ተሰብሮ የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል።

3ኛ. በ24/07/2002 ዓ.ም. ባናራ ቀበሌ የክልል ዕጩ የሆኑት አቶ ታደሰ ቢንጫሞ እና አቶ አንዴሙ ዘውዴ እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አቶ አጫሙ ቦቄ የድብደባ ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል።

4ኛ. በደቡብ ሃድያ ዞን ዱና ወረዳ፤ በአንሾና ውሃ ገበታ፣ በቡራ ቡርሻና በኢናራ ቀበሌ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አባሎቻችን እንዳያደርጉ ክልከላ ተፈፅሟል።

5ኛ. በምዕራብ ወለጋ ዞን በ27/07/2002 ዓ.ም. የአባላቶቻችን የተፈቀደ ስብሰባ በብጥበጣ እንዲበተን ተደርጎል።

6ኛ. በዚሁ በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ በ28/07/2002 ዓ.ም. ተመሳሳይ ብጥበጣ ተካሄዶ፤ አባላቶቻችን በአዳራሽ ውስጥ የጀመሩት ስብሰባ ተበትኗል። በወቅቱ በጥባጮቹ ከፖሊስ አቅም በላይ የሆነ ችግር ፈጥረዋል ተብሎ ሪፖርት የቀረበ ቢሆንም፤ ለአባሎቻችን ምንም ዓይነት የሕግ ከለላ ሳይደረግላቸው ቀርቷል። በሌላ በኩል ጉቴ ኑሌ ካባ ቁጥር 2 የምርጫ ክልል ሰዬ ደበሶ በሚባል ወረዳ ውስጥ አስመስሎ በተዘጋጀ የኦፌዲን (የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ማህተም “ግብር አትክፈሉ” የሚልና ድርጅታችንን ከመንግሥትና ከሀገሪቱ ሕግ ጋር የሚያላትም … ተግባር ተፈፅሞ፤ በዚሁ ሳቢያ በርካታ የኦፌዲን አባሎች ያልፈፀሙትን ተግባር “ፈፅማችኋል” በሚል በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ ይገኛሉ።

በዚሁ ደበሶ ከተማ በ24/07/2002 ዓ.ም. ምሽት የድርጅታችን አባል በሆነው ደገፉ ረጋሳ የመኖሪያ ቤት በር ላይ የኦህዲድን መፈክር ለመለጠፍ ሙከራ ሲደረግ፤ አባሉ “አባል ያልሆንኩበት ድርጅት መፈክር በሬ ላይ አይለጠፍም” በማለቱ እስከ ዛሬ ተይዞ በእስር ላይ ይገኛል።

7ኛ. በአጠቃላይ በመላ ሀገሪቱ የመንግሥት ሠራተኞችን በሚመለከት፤ ለምርጫ ቅስቀሳ ሥራ ከመጠቀም አንስቶ ፎርም አዘጋጅቶ በማስሞላት ኢህአዲግን እንዲመርጡ የማስገደድ ተግባር ተጧጡፎ ቀጥሏል። ስምንት ፓርቲዎችን ያቀፈው መድረክ በተጨባጭ ማስረጃ አላቸው ያላቸውን የዕጩዎችና የአባላት እንግልት ይፋ አውጥቷል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ