“እሳት ለኩሶ በሕፃናት ደም መጫወት አይቻልም” ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ

“የሕፃናትን ደም ያፈሰሰው ህወሓት/ኢህአዲግ ነው” ተቃዋሚዎች

Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 6 ቀን 2002 ዓ.ም. April 14, 2010)፦ ማክሰኞ ሚያዝያ 5 ቀን 2002 ዓ.ም. ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ፓርላማ ተገኝተው ያቀረቡትን መንግሥታዊ ሪፖርት፣ ተቃዋሚዎች “ተራ ማስታወሻ እና ስድ ንባብ ነው” በማለት አጣጣሉት።

 

ሪፖርቱን ያጣጣሉት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አቶ ለገሰ ቢራቱ እና አቶ ልደቱ አያሌው ሲሆኑ፤ ዶ/ር መራራ ጉዲና “ምርጫው በሠላማዊና በፍትሃዊ መንገድ ላለመጠናቀቁ ምልክቶች እየታዩ ነው” ብለዋል። አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው ደግሞ ”ኢትዮጵያ 11 በመቶ ዕድገት አስመዝግባለች ብሎ ማለቱ ከኢህአዲግ ባዶ ጩኸት አይለይም” ሲሉ ገልጸዋል።

 

አቶ ተመስገን ዘውዴ “የዋጋ ግሽበትን እንዲቀንስ አድርገናል የሚባለው የምጣኔ ሀብት መገምገሚያ መስፈርቶችን ግንዛቤ ውስጥ ባላስገባ ተራ ስሌት ነው” ሲሉ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊን “የ3 በመቶ የዋጋ ግሽበት ዝቅ ብሏል” ሪፖርት አጣጥለውታል። ከመቼውም ጊዜ በላይ በተቃዋሚዎች ላይ የኢህአዲግ ፓርላማ አባላት ሳቅና ፌዝ ባሳዩበት በማክሰኞው የፓርላማ ውሎ፤ የህወሓት ሊቀመንበርና ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቀጥተኛና አሳማኝ መልስ ከመስጠት ይልቅ ነገሮቹን ሁሉ ሲያቃልሉ፣ ሲያለባብሱና ተቃዋሚዎቻቸውንም አብዝተው ሲያስጠነቅቁ ተስተውለዋል።

 

አቶ ልደቱ አያሌው ያቀረቡትን የ“ተበድያለሁ” አቤቱታ የሰሙ መሆናቸውን የገለጹት ጠ/ሚ መለስ፤ አቶ ልደቱ አያሌው ባጋጠማቸው ችግር ያዘኑ መሆናቸውን፣ መረጃ ካገኙም “የኢህአዲግ አዋራጆች …” ያሏቸውን አንዳንድ የፓርቲያቸውን ሰዎች ከአባልነት እስከማባረር የሚዘልቅ ርምጃ በመውሰድ እንደሚቀጡ በፓርላማው ፊት ቃል ገብተዋል።

 

“የምርጫ መወዳደሪያ ዓርማን የቀደደ ሰው ሽፍታ ነው” ያሉት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ ኃይማኖት ላይ መሰረት ያደረገ ቅስቀሳ “የቆሸሸና የሻገተ የአድሃሪያን ተግባር በመሆኑ አንታገሰውም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

 

በኦሮሚያ ክልል … አባሎቻችን በምርጫ ቦርድ ሰዎች ፊት ተይዘው ታስረውብናል። ኢህአዲግ በራሱ ካድሬዎች ቁጥጥር ሥር በዋለ ስቱዲዮ የምርጫ ክርክሩን ማድረጉም ተገቢ አይደለም … ይህን የመሰለው ወንጀል ሁሉ ኢህአዲግን በሥነ-ምግባር ደንቡ መሠረት ተጠያቂ አድርጎ ከምርጫው ተሳትፎ ውጪ ሊያደርገው በቻለ ነበር …” በማለት ዶ/ር መራራ ጉዲና ላቀረቡት አቤቱታና በሚሊዮን የሚቆጠር ምስክር እናቀርብበታለን ላሉት ጉዳይ፤ ጠ/ሚ መለስ “አሁንም ቢሆን የጥፋት ግንባሮችንና የተባባሪዎቻቸውን ንቅናቄ በቸልታ አንመለከትም። የኢህአዲግ አቋም በጥፋት ግንባሮች አመለካከት ላይ የሚለወጥ አይደለም። እርስ በርሳችሁ እየተደባደባችሁ ለአቤቱታ መሮጡን ተውት! ከእንዲህ እሳት ለኩሶ ሸርተት ማለት እና በሕፃናት ደም መጫወት አይቻልም። ... ያለው አንድ መንገድ ሠላማዊና ሕጋዊነት ብቻ ነው። ሕጋዊውን ከሕገ-ወጡ እያቀላቀሉ እንዳለፈው ጊዜ መጓዝ የሚቻልበት መንገድ ተዘግቷል” በማለት ነበር ማስፈራሪያ አዘል ምላሻቸውን የሰጡት።

 

ጠ/ሚ መለስ ይህን ቢሉም “በምርጫ 97 የሕፃናትን ደም ያፈሰሰው …፣ በሕግ እና በሕግ አስከባሪነት ስም የህዝቡን ድምፅ የነጠቀው ህወሓት/ኢህአዲግ ነው …” በማለት ተቃዋሚዎች መልስ ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ