Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2002 ዓ.ም. April 26, 2010)፦ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በዕጩዎቹና በአባላቶቹ ላይ ከፍተኛ ወከባና እንግልት እየተፈጸመ መሆኑን ገለጸ።

 

መድረክ በዕጩ ተወዳዳሪዎቻችን ላይ ያነጣጠሩና የሥነ-ምግባር ደንቡን የሚፃረሩ፤ የማስፈራሪያ፣ የማሸማቀቂያና የሥነ-ልቦና ሰለባ ዘመቻዎች በኢህአዴግና በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ እየተደረገብኝ ነው በማለት “ሕገ-መንግሥቱን፣ የምርጫ ሕጉንና የሥነ-ምግባር ደንቡን በመጣስ በመድረክ ዕጩዎች፣ አባላትና በመራጩ ህዝብ ላይ እየተሰነዘረ ያለው ሕገ-ወጥ ርምጃ ይቁም!” የሚል ባለ 6 ገጽ መግለጫ አወጣ።

 

መግለጫውም በመድረክና በአባል ድርጅቱ ላይ ተፈጽሟል ያላቸውን በደሎች ከ22 በበለጡ ነጥቦች በዝርዝር አስቀምጧል። ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ከአንድ ሣምንት የበለጠ ጊዜ ያስቆጠረው የአውሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድንም እስካሁን የሠራውን ሥራ አላየንም፤ ሲል መድረክ ቅሬታውን ሰንዝሯል። ሚያዝያ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. 6 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ በር ፊት ለፊት በሚገኘው ጽ/ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጠው መድረክ፤ “የምርጫውን ሂደት የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ስለመሆናቸው የሚያሳዩትን ተጨባጭ ማስረጃዎች ብናቀርብለትም የምርጫ ቦርድ የሰጠን ምላሽ ቀዝቃዛ ነው” በማለት ቦርዱን ወቅሷል።

 

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እና አቶ አስራት ጣሴ በመግለጫው ላይ ተገኝተው በሠላማዊ መንገድ በምርጫው ተሳትፎ እያደረግን እንዳንቀጥል የሚያውኩን ነገሮች ሁሉ ይወገዱልን፣ ጠ/ሚንስትር መለስ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንቡን በመጣስ ከሚሰነዝሩት የዛቻና የማስፈራሪያ ቃላት ይታቀቡልን፣ … ብለዋል። በባሌ፣ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በአማራው ክልል እንደዚሁም በከንባታ አላባ ጠንባሮ፣ በሃዲያና በአብዛኞቹ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በዕጩዎቹ እና በአባል ደጋፊዎቹ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና በሀገሪቱ ገዥው ፓርቲ ብቻ እንዲመረጥ ቁርጠኛ ፍላጎት ያለ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነውም ሲሉ የመድረኩ አመራሮች አክለው ገልጸዋል።

 

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ጥቅሙ ምን እንደሆን በግልጽ ባያብራሩም “የአውሮጳ ሕብረት ታዛቢ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ወዲህ አቤቱታችንን አልተመለከተም፤ የራሱን ጥቅም ከማስቀደም ውጪ የሠራውን ሥራ በተግባር አላየንም” ብለዋል። ( መድረክ ያወጣውን ባለስድስት ገጽ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ