Prof. Beyene ፕ/ር በየነ ጴጥሮስEthiopia Zare (ሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2002 ዓ.ም. April 26, 2010)፦ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የመድረኩ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ”ሕገ መንግሥቱን የሚፃረርና ኹከት የመፍጠር አዝማሚያ ያለው ንግግር አድርገዋል” በማለት ዛሬ ማምሻውን መግለጫ አወጣባቸው። መግለጫው ”ሕግ የጣሰ ነው” ያለውን የፕ/ሩን ንግግርም ሆነ ወደፊት በሚደረጉ ተመሳሳይ ንግግሮችና መግለጫዎች ላይ እርምጃ እንወስዳለን ይላል።

 

ይኸው የኢህአዴግ መግለጫ፤ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ”ቃል ገብቶ ተግባራዊ ማድረግ ያቃተውን ፓርቲ ህዝቡ ያወርደዋል፤ እንዲያውም አምስት ዓመት አይቆይም” በማለት ለደጋፊዎቻቸውና ለአባላቶቻቸው ተናግረዋል፤ ፕሮፌሠሩ በዚህ ንግግራቸው የአመጽ መንገድን ሰብከዋል፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝነታቸውን አላሳዩም ሲል ይወነጅላቸዋል።

 

መግለጫው አክሎም ይህ የፕ/ር በየነ ንግግር ሕገ መንግሥታዊ አሠራሩን የሚጋፋና በተሸፋፈነ መንገድ ኹከት የመፍጠር አዝማሚያ ያለው ነው ይላል። እናም ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ እንደሚያምንና ለዚያም እየሠራ እንደሆነ መግለጫው ያትትና፤ ከዚህ ውጭ በአመጽ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ኢህአዴግ አጥብቆ እንደሚታገለው ይገልፃል።

 

ይኸው ምርጫው ሊካሄድ 26 ቀናት ሲቀሩት ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2002 ዓ.ም. ማምሻውን የወጣው የኢህአዴግ ማስጠንቀቂያ እንደሚለው ከሆነ፣ ”ሕግ የጣሰ ነው” ያለውን የፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ንግግርም ሆነ ወደፊት በሚደረጉ ተመሳሳይ ንግግሮችና መግለጫዎች ላይ እርምጃ እንወስዳለን ሲል አስጠንቅቋል።

 

ባለፈው ሚያዝያ 5 ቀን ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) መንግሥታዊ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ “... አሁንም ቢሆን የጥፋት ግንባሮችንና የተባባሪዎቻቸውን ንቅናቄ በቸልታ አንመለከትም። የኢህአዲግ አቋም በጥፋት ግንባሮች አመለካከት ላይ የሚለወጥ አይደለም። እርስ በርሳችሁ እየተደባደባችሁ ለአቤቱታ መሮጡን ተዉት! ከእንዲህ እሳት ለኩሶ ሸርተት ማለት እና በሕፃናት ደም መጫወት አይቻልም። ... ያለው አንድ መንገድ ሠላማዊና ሕጋዊነት ብቻ ነው። ሕጋዊውን ከሕገ-ወጡ እያቀላቀሉ እንዳለፈው ጊዜ መጓዝ የሚቻልበት መንገድ ተዘግቷል ...” በማለት ነበር ማስፈራሪያ አዘል ንግግር ማድረጋቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

 

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 19 ዓመታት በብቸኝነት ኢትዮጵያን እየገዛ ያለ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ