Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. May 9, 2010)፦ በዛሬው ዕለት የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን በመጥቀስ፤ ”በመድረክ ፓርቲ የተደራጁ ሦስት ግለሰቦች አንድ ፖሊስ በአሰቃቂ ሁኔታ በጩቤ ወግተው ገደሉ” በማለት መዘገባቸው ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አስረዳ።

 

እነኝሁ ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ካለገደብ በብቸኝነት የሚገለገልባቸው የመንግሥት (የህዝብ) መገናኛ ብዙኀን የኦሮሚያን ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ ጠቅሰው ነው ዘገባውን ያስተላለፉት። ኮሚሽኑ የመድረክ ፓርቲ አባላቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ትናንት ሚያዝያ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. በጩቤ ገደሉት በማለት በመግለጫው ያወጣው የፖሊስ ባልደረባ የነበረውን ኮንስታብል ሐሰን ረጋሳን ነው።

 

ይኸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ፤ በምዕራብ ሸዋ ልዩ ስሙ ”ዒሉ ገላን” በተባለ ወረዳ፣ ቀበሌ 01 ውስጥ የፖሊስ ባልደረባው መገደሉን ጠቅሶ፤ ገዳዮቹ የመድረክ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ታሪኩ ጌታቸው፣ በአቶ ብርሃኑ ሸንተሙ እና ፍሮምሳ ቦጋለ ማለቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

 

ይኸው መግለጫ ግድያውን የፈፀሙት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ጉዳዩ እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጿል።

 

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ መድረክን የወነጀለ ሲሆን፣ ”መድረክ ሆን ብሎ መመሪያ በመስጠት ከሚያደርገው ሕገወጥና አፍራሽ ድርጊት እንዲቆጠብ” በማለት ማሳሰቢያ መስጠቱን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያስረዳል።

 

ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በጉዳዩ ላይ የመድረክ ፓርቲ ምንም አይነት ኦፊሴላዊ መግለጫ አለመስጠቱ ታውቋል።

 

ገዥው ፓርቲ የዘንድሮውን ምርጫ አስመልክቶ በተደጋጋሚ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያስጠነቀቀ ሲሆን፣ በተለይም ትኩረቱን በመድረክ ፓርቲ ላይ ማድረጉን በተከታታይ ካወጣቸው መግለጫዎች ለመረዳት ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ