በዕጩዎች ላይ የሚደረገው ድብደባና ወከባ ተባብሷል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. May 15, 2010)፦ 4ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ 8 ቀናት የቀረ ሲሆን፣ በተቃዋሚ ዕጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚደርሰው ድብደባና ወከባ መባባሱ ተገለጸ።
ስምንት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያቀፈው መድረክ ዕጩ ተመራጮቹ ከፍተኛ ወከባና የጥላቻ ዘመቻዎች በመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን እየደረሱበት መሆኑን በተደጋጋሚ ከመግለጹም በላይ፣ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ/መድረክ ዕጩ ተወዳዳሪ የሆነው አቶ ሠለሞን ባልቻ በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ፤ ሚያዝያ 16 ቀን በአካባቢ የሚሊሺያ ዘርፍ አባላት ተደብድቦ ሞቷል ተብሎ ከተጣለ በኋለ ሰብዓዊነት በሚሰማቸው ወገኖቹ ከወደቀበት ሥፍራ ተነስቶ በድጋፍ ሰውነቱን እየጐተተ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ሠለሞን ባልቻ “... ዕጩ ተወዳዳሪ ከመሆኔ ውጪ በታጣቂዎች ሊያስደበድበኝ የሚችል አንድም ዓይነት ጥፋት አልፈጸምኩም …” ሲል መግለጫ ሰጥቷል። ሙሊሳ ተሾመ የተባለው የኦህኮ/መድረክ ዕጩ ተወዳዳሪ እና የፓርቲው አባል የሆነው አቶ ደምሴ ሸቡ ደግሞ ቅዳሜ ሚያዝያ 23 ቀን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ቶሌ ወረዳ ባንቱ ከተማ ውስጥ ከረፋዱ 4 ሰዓት በታጣቂዎች ክፉኛ ተደብድበው በግልጽ በአናታቸውና በአገጫቸው እንዲሁም በግንባራቸው ላይ ተፈንክተው ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን ፓርቲው አስታውቋል።
ሌላው በምዕራብ ሸዋ አዳ-በርጋ ሚያዝያ 23 ቀን 2002 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ የኦህኮ/መድረክ አባል አቶ ቶኩማ ደሜም ጭንቅላቱ ላይ ተደብድቦ በስቃይ እንደሚገኝ ተገልጿል። ስማቸው የተገለጸው አራቱ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ የመድረክ ጽ/ቤት ተገኝተው ለአውሮፓ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን አባላትና ለአንዳንድ ጋዜጠኞች ቃላቸውን ሰጥተዋል። በአካላቸው ላይ የደረሰውን ጉዳትም አሳይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦህዲድ/ኢህአዲግ “አባሌ ነው” ሲል ከመድረክ ጋር የተወዛገበበትና “በድብደባ ላለመሞቱ ማስረጃ አለኝ” ሲል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠበት በሜዳ-ቀኝ ወረዳ የኦፌዲን አባል የነበረው የሟች ቢየንሳ ጋዲሣ ወላጅ አባትና ወንድሙ አዲስ አበባ ተገኝተው ለአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሠራተኞችና ለአውሮፓው ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን ቢየንሳ በደረሰበት ድብደባ ምክንያት መሞቱን በማረጋገጥ ምስክርነት መስጠታቸውን ከመድረክ ጽ/ቤት ያገኘነው ማስረጃ ያመለክታል።



