መድረክ በመስቀል አደባባይ የጠራው ስብሰባ ተከለከለ
በደብረዘይትና በአዲስ አበባ የመጨረሻ ቅስቀሳውን ያካሂዳል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. May 15, 2010)፦ መድረክ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. (ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም.ትን በማሰብ) በመስቀል አደባባይ ሊጠራው ያሰበው ህዝባዊ ስብሰባ ሳይሳካ ቀረ።
ጥሪው ያልተሳካው የአዲስ አበባ አስተዳደር የህዝባዊ ስብሰባዎች ፈቃድ ሰጪ ክፍል “በአደባባይ ስብሰባ ማድረግ አይቻልም” የሚል ምላሽ በመስጠቱ መሆኑ ታውቋል። ፈቃድ ሰጪው አካል ለእሁድ ግንቦት 8 ቀን 2002 ዓ.ም. መድረክ በአዲስ አበባ ስታዲየም ስብሰባ የመጥራት መብት አለው ቢልም፤ በዕለቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስፖርታዊ ውድድር ዝግጅት አለኝ በማለቱ፤ መድረክ ለእሁድ ከቀትር በኋላ ያቀደው ስብሰባም ከሽፎበታል።
በዚህም ምክንያት “ሰበቦችን በመደርደር ኢህአዲግ ደንቃራ ሆኖብኛል። የአደባባይ ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማ ማካሄድ አልቻልኩም። ይህም ሊሆን የቻለው ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ዲሞክራሲያዊ፣ … ምርጫ አካሂዳለሁ በሚለው አካል መሆኑ ያሳዝናል” ሲል በአቶ መለስ የሚመራውን ገዢ ፓርቲና ድርጊቱን ኮንኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ መድረክ የመጨረሻ ይሆናል ያለውን የአዳራሽ ስብሰባ በደብረዘይት ከተማ የሚያካሂድ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በ10 ተሽከርካሪዎች የታገዘ የመንደር ለመንደር ቅስቀሳም ዛሬ ግንቦት 7 ቀን በመላው አዲስ አበባ ለማካሄድ መዘጋጀቱንም የ8ቱ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መድረክ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው የመጨረሻ ቀን ቅስቀሳ “ግንቦት 7ትን አስታውሱ! የግንቦት ሰባትን ታሪክ ድገሙ!” የሚል ልዩ መርኅ አለው። በሌላ በኩል ምርጫ 2002ትን አስመልክቶ የተገኘው ቅድመ መረጃ የጠቆመው፤ ከነገ እሁድ ግንቦት 8 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውንም የአዳራሽም ይሁን የአደባባይ የምረጡኝ ቅስቀሳ ተቃዋሚዎች ማካሄድ እንደማይችሉ ነው።



