በተንቤን የአቶ ስየ ቅስቀሳ ችግር ገጥሞታል

ወ/ሮ አረጋሽ በአድዋ የጠሩት ስብሰባ ብጥብጥ አስነሳ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 12 ቀን 2002 ዓ.ም. May 20, 2010)፦ ከሦስት ቀናት በኋላ ከፍተኛ የ‘ምርጫ’ ፉክክር ይካሄድበታል ተብሎ በሚጠበቀው በትግራይ ክልል በተምቤን እና አድዋ ወረዳዎች አቶ ስየ አብርሃ እና ወ/ሮ አረጋሽ በሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ከፍተኛ ወከባ እየገጠማቸው መሆኑን ገለጹ።
አቶ ስየ እሳቸውንና ፓርቲያቸውን የሚደግፉ ሰዎችን የህወሓት/ኢህአዲግ ታጣቂዎች ከማስፈራራት አልፈው “ስየ ነፍጠኞችንና የደርግ ርዝራዣችን ይዞ እየመጣብህ ነው …” በማለት የተምቤንን ህዝብ እያወናበዱ እንደሚገኙ ለጋዜጠኞችና ለፓርቲያቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸው፤ “በእኔና በቤተሰቦቼ ላይ ግልጽ ዛቻና ማስፈራራት እየተሰነዘረብን ቢሆንም፤ የምርጫ ቅስቀሳዬን እስከመጨረሻው እቀጥላለሁ” ማለታቸው ታውቋል።
በዐድዋ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ለምርጫ ቅስቀሳ አደባባይ በወጡበት አጋጣሚ ሁለት ተሽከርካሪዎቻቸው በድንጋይ እንደተሰባበሩና ህዝባዊ ስብሰባ በጠሩበት አዳራሽ ህወሓት በላካቸው ጠብ ቆስቋሽ ወጣቶች ህዝቡን እያነጋገሩ የነበሩበት አዳራሽ ወደ ጠብ መድረክነት የመለወጥ አዝማሚያ በማሳየቱ ስብሰባውን ለማቋረጥ ተገድደዋል። ጉዳዩን ለፖሊስ ቢያሳውቁም ፖሊስ ጠብ ቆስቋሾቹን ወጣቶች በቁጥጥር ስር ለማዋልና የጠሩት ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይታወክ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን እንዳላሳየ ወ/ሮ አረጋሽ ተናግረዋል።
የቀድሞዋ የህወሓት ታጋይ ዐድዋ ውስጥ ዓረና/መድረክን በመወከል በሚያደርጉት ሠላማዊ እንቅስቃሴ ከተቃዋሚዎች ጋር በመተባበር ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን እንደሚፎካከሩ ይታወቃል።
የምርጫ ቅስቀሳው ከዛሬ ጀምሮ እንደሚቆም የምርጫ ቦርዱ ሕግ እንደሚያዝ ተገልጿል።



