Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም 13 ቀን 2004 ዓ.ም. September 24, 2011)፦ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱአለም አራጌ፣ የኦፌዴን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦህኮ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንንና አቶ አሳምነው ብርሀኑ፣ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፣ ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ፣ ጋዜጠኛ ስለሽ ሐጎስ እንዲሁም አርቲስት ደበበ እሸቱ የአንባገነናዊው ሥርዓት ጅምላ እስራት ሰለባ ከሆኑት ጥቂቶቹ መሆናቸውን መድረክ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዛሬ በላከው መግለጫ ገለፀ።

 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በቅርቡ በ”ሽብርተኝነት” ስም እየታሰሩ ያሉትንና በሠላማዊ ትግልና በጋዜጠኝነት እየሠሩ ያሉትን ግለሰቦች አስመልክቶ ”በሽብርተኝነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!” በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል።

 

ታሳሪዎቹ በሀገሪቱ በሚደረገው ፈታኝ ሠላማዊ ትግል ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ ጥላ ስር ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑ ፖለቲከኞችና ሞያዊ ግዴታቸውን አክብረው ለህዝብ ትክክለኛና ያልተዛባ መረጃ ለማድረስ የሚተጉ ጋዜጠኞች መሆናቸውን መድረክ አጥብቆ እንደሚያምን ገልጿል። ኢህአዴግ በሽብርተኝነት ወንጀል ስለመታሰራቸው በመገናኛ ብዙኀን ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጭ እንጂ ስለፈፀሙት የሽብር ተግባር ተጨባጭ ማስረጃ ሲያቀርብ አለመታየቱን መድረክ ገልጿል።

 

መግለጫው ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤ የሁሉም የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች ሰብዓዊ-መብት መከበሩና በአስቸዃይ እንዲረጋገጥ፤ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ ስም የሚደረገው የህዝብ መብት ረገጣና እስራት በአስቸዃይ እንዲቆም፤ ህዝብን አፍኖ ለመግዛት ታስቦ የተዘጋጀው “የፀረ-ሽብርተኝነት” አዋጅ ከበርካታ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሻር፤ እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ በወንጀል ተጠርጥሮ እስካልተፈረደበት ድረስ እንደወንጀለኛ ያለመታየት ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው ይታወቃል። በመሆኑም የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ፍርድ ባልተሰጠባቸው ዜጎች ላይ እንደተፈረደባቸው ወንጀለኞች በመቁጠር የሚያሰራጩትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስቧል።

 

በመጨረሻም ”በሽብርተኝነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!” ሲል መድረኩ ያለውን አቋም ገልጿል። መድረክ ያወጣው ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ቀርቧል።

 

በሽብርተኝነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም! 

ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ

በሰላማዊ ትግል ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉ ሰላማዊ ዜጎችን አግባብ ባልሆነና ባልተጨበጠ ክስና ውንጀላ ማሰር፣ አፍኖ መሰወር፣ ንብረትን ማውደምና መውረስ እንዲሁም የአደባባይ ግድያ ባለፉት 20 የኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመናት የተለመዱ ተግባሮች ሆነው ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ይህ አምባገነናዊና ኢፍትሀዊ ተግባር በሕግ ሽፋን ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለገዥው ሥርዓት የአፈናና የጥርነፋ መዋቅር ተባባሪ ያልሆኑና ለመብታቸው መከበር የሚታገሉ ዜጎች በአሸባሪነት ስም በጅምላ እየታፈሱና እየታሰሩ ይገኛሉ። ታፍነው የተወሰዱና ያሉበት ቦታ የማይታወቀውም ጥቂት አይደሉም።

 

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ታስረዋል። ሰብዓዊ መብታቸውም በማንአለብኝነት እየተረገጠ ይገኛል። ከነዚህ ንፁሀን ዜጎች ውስጥ ብዙዎቹ የመድረክ አባላቶችና ለሞያቸው ታማኝ የሆኑ ጋዜጠኞች መሆናቸውን ስናይ ደግሞ ዘመቻው በሀገራችን ተጠናክሮ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ለመጨፍለቅና ህዝብን ከትክክለኛ መረጃ አርቆና አፍኖ ለመግዛት ታስቦበትና ሆነ ተብሎ የተያዘ ስልት መሆኑን እንገነዘባለን።

 

የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱአለም አራጌ፣ የኦፌዴን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦህኮ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንንና አቶ አሳምነው ብርሀኑ፣ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፣ ጋዜጠኛ ሪዮት አለሙ፣ ጋዜጠኛ ስለሽ ሐጎስ እንዲሁም አርቲስት ደበበ እሸቱ የአንባገነናዊው ሥርዓት ጅምላ እስራት ሰለባ ከሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።

 

እነዚህ ዜጎች በሀገራችን በሚደረገው ፈታኝ ሰላማዊ ትግል ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ ጥላ ስር ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑ ፖለቲከኞችና ሞያዊ ግዴታቸውን አክብረው ለህዝብ ትክክለኛና ያልተዛባ መረጃ ለማድረስ የሚተጉ ጋዜጠኖች መሆናቸውን መድረክ አጥብቆ ያምናል።

 

ለእስር የዳረጋቸው መንግሥትም በሽብርተኝነት ወንጀል ስለመታሰራቸው በመገናኛ ብዙሃን ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጭ እንጂ ስለፈፀሙት የሽብር ተግባር ተጨባጭ ማስረጃ ሲያቀርብ አልታየም።

 

በመሆኑም፦

1ኛ. ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤

2ኛ. የሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ሰብዓዊ-መብት መከበሩ በአስቸዃይ እንዲረጋገጥ፤

3ኛ. በፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ ስም የሚደረገው የህዝብ መብት ረገጣና እስራት በአስቸዃይ እንዲቆም፤

4ኛ. ህዝብን አፍኖ ለመግዛት ታስቦ የተዘጋጀው “የፀረ-ሽብርተኝነት” አዋጅ ከብርካታ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሻር፤ እንዲሁም

5ኛ. ማንኛውም ዜጋ በወንጀል ተጠርጥሮ እስካልተፈረደበት ድረስ እንደወንጀለኛ ያለመታየት ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው ይታወቃል። በመሆኑም የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ፍርድ ባልተሰጠባቸው ዜጎች ላይ እንደተፈረደባቸው ወንጀለኞች በመቁጠር የሚያሰራጩትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሁሉ መልዕክቱን ያስተላልፋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለማስከበር ከፓርቲያችን ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

 

መንግሥት በፈረጠመ አምባገነናዊ ክንድ ህዝብን በማፈን የስልጣን ዘመንን ለማራዘም መሞከር አወዳደቅን ማክፋት መሆኑን ካለፉት አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሊማር ይገባል!

 

በሽብርተኝነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!

ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)

መስከረም 09 ቀን 2004 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ