እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ
እስረኞቹ ከአንድ ወር በኋላ ቤተሰቦቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ አይተዋል
Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም. October 13, 2011)፦ በማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የተወሰደባቸውና በሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸው እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዷለም አራጌና ሌሎች እስረኞች በድጋሚ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ተመልሰዋል።
ለዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት እንዲቀርቡ ቀጠሮ የተሰጣቸው ቢሆንም፤ የፍርድ ቤቱ የቀጠሮ ሰዓት ተቀይሮ በ3 ሰዓት ጋዜጠኞችና ቤተሰቦች ባልተገኙበት እንዲቀርቡ መደረጉን ለማወቅ ችለናል።
እስረኞቹ ውስጥ ጋዜጠኛ እስክንር ነጋ እና አቶ ዘመኑ ሞላ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች የገለጹ ሲሆን፤ የሌሎቹን ሦስት እስረኞች ማንነት ለማወቅ ባይቻልም፤ አቶ አንዷለም አራጌ፣ አሳምነው ብርሃኑና ናትናኤል መኮንን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ተችሏል።
ለከሰዓት በኋላው የስምንት ሰዓቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ዝግጅት እያደረጉ ከነበሩት የእስረኞቹ ቤተሰቦች ጠዋት በፍርድ ቤት አካባቢ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንና በአስቸኳይ እንዲደርሱ ጥሪ ከደረሳቸው መካከል የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት አንዷ ነች። ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በቦታው ለመድረስ እንደቻለች እና በጥበቃው ሁኔታ አካባቢው ተወጥሮ ስለነበር እስረኞቹን ማየት እንዳልቻለች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጻለች።
ጋዜጠኛ ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል ከአንድ ወር በኋላ ትላንት ባለቤቷን ለማየት እንደቻለች በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ የገለጸች ሲሆን፤ የባለቤቷ ሰውነት በጣም ከመክሳቱ ውጭ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ገልጻለች። ጋዜጠኛ ሰርካለም ወደ እስር ቤት ዕለታዊ ስንቅ ለማቅረብ በቀረበች ሰዓት እንድትጠይቀው መፈቀዱንና በቢሮ ተጠርቶ እንዳነጋገራት ገልጻለች። በጊዜው ሌሎች ቤተሰቦችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲጎበኙ ተደርጓል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ምንም አይነት ድብደባ እንዳልደረሰበት ለባለቤቱ የገለጸ ሲሆን፣ ሰውነቱ ከሚገባው በላይ ከስቶ ማየቷን ገልጻለች። በፖሊሶችም ለዛሬ 8 ሰዓት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ለጋዜጠኛ ሰርካለም የተነገራት ቢሆንም፤ ባልታሰበ ሰዓት ጠዋት ሦስት ሰዓት እንደሚቀርቡ በሰማች ሰዓት በቦታው እንደደረሰች አካባቢው በወታደሮች ተከቦ ወደ ውስጥ መግባትም መውጣትም በማይቻልበት ሁኔታ ማግኘቷን ገልጻለች።
በስምንት ሰዓት የተሰጠ ቀጠሮ በምን ሁኔታ ጠዋት ሊታይ ይችላል በማለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡ ጋዜጠኞች የጊዜ ቀጠሮ በማናቸውም ሰዓት መታየት ይችላል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
ባለፈው ሣምንት ሐሙስ አርቲስት ደበበ እሸቱ እና አቶ ውብሸት ፍርድ ቤት ቀርበው በተመሳሳይ የ28 ቀን ቀነ ቀጠሮ ተወስዶባቸው ወደ እስር ቤት ማምራታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ጋዜጠኞችና ቤተሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው ችሎቱን መከታተል ችለው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።



