በታክሲ ፍንዳታው የሞቱት ስድስት ናቸው
• የአራተኛው አስከሬን በማግሥቱ በሼህ አላሙዲን መናፈሻ ውስጥ ተለቅሞ ተገኘ
• 5ኛውና 6ኛው አካላቸው ተቆራርጦ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ አርፈዋል
• አንዱ በትውልድ እስራኤላዊ በዜግነቱ አሜሪካዊ ነው
Ethiopia Zare (ኀሙስ ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. May 22, 2008)፦ ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ወደ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ በአዲስ አበባ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጎን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት በር ላይ በሚኒባስ ታክሲ ላይ በደረሰው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ስድስት መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ገለጠ።
በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ፍንዳታው እጅግ ከፍተኛ እንደነበር አረጋግጠዋል። እስከዛሬ ከደረሱት ፍንዳታዎች ውስጥ ይኸኛው የተለየና እጅግ ዘግናኝ እንደነበር የዓይን እማኞች ለኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
እንደነኝሁ እማኞች ገለጻ ከሆነ የሟቾች አስከሬን በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳቱ እስከመለቀም ደረጃ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ በሕይወት የተገኙት ዘጠኙም ቢሆኑ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሶባቸው ስለነበር ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስደው ነበር።
ፍንዳታው በተከሰተ ምሽት ሦስት ሰዎች መሞታቸውንና ሁለቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መዘገባችን አይዘነጋም። ሦስቱም ሟቾች ወንዶች ናቸው። ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት ውስጥ ሁለቱ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበረ በመሆኑ በሆስፒታሉ አድረዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ የሕክምና እርዳታ አግኝተው ወደቤታቸው ሄደዋል።
ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተወሰዱት አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ሲሆኑ፣ ሁለቱም በማግስቱ ሆስፒታል እንደተኙ ሕይወታቸው አልፏል። ሁለቱም በአካላቸው ላይ ከፍተኛ የመቆራረጥ ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር ለማወቅ ችለናል። ከእነዚህ ሁለቱ ውስጥ ወንድየው በትውልድ እስራኤላዊ፣ በዜግነት አሜሪካዊ የነበረው ፕሮፌሰር ሴሄሽክሪ ሾስለኒ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በፍንዳታው ከፍተኛነት የተነሳና በደረሰው አሰቃቂ ጉዳት የተነሳ አካባቢው በቁርጥራጭ የሰው ሥጋ ተሞልቶ ስለነበር፣ በማግስቱ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ.ም. የፖሊስ ባለሙያዎች አካባቢውን ሲፈትሹ፣ ሲያጣሩና ፍለጋ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። በዚሁ ፍለጋቸውም የሼህ መሐመድ አላ ሙዲ ንብረት በሆነውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና በሂልተን መሃከል በሚገኘው መናፈሻ ውስጥ የአንድ ሰው አካል ቁርጥራጭ ፖሊሶች ማግኘታቸው ታውቋል።
በፍንዳታው ዕለት ሦስት፣ በማግስቱ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል። በሚኒባስ ታክሲው ውስጥ አሽከርካሪውን ጨምሮ አስራ አራት ሰዎች ተሳፍረው ነበር። ከተራፊዎቹ ውስጥ የታክሲው አሽከርካሪ እንደሚገኝበት ለማረጋገጥ ችለናል። ሚኒባስዋ ከጥቅም ውጪ ስትሆን በእሳት ጋይታለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን ድረስ የፍንዳታውን ኃላፊነት የወሰደ አካልና ወገን አለመኖሩ ታውቋል።



