አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል እና ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ መሰብሰብ አቁመዋል

ሰኔ ሰባት ጠቅላላ ጉባዔው ይካሄዳል

Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2000 ዓ.ም. May 30, 2008)፦ በሀገራችን የምርጫ እና የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በማይረሳው ምርጫ 97 ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የ“ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ” አመራሮች እና የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ሲከፋፈሉ መሰንበታቸው አይዘነጋም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አመራሮቹና የላዕላይ ምክር ቤቱ አባላት አሁን በስተመጨረሻ ክፍፍሉ መስመር እየያዘና እየጠራ በመምጣት ላይ እንደሚገኝ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

የክፍፍሉ ሂደት

በምርጫ 97 ማግስት በእነ ልደቱ አያሌው ጊዜ ለሁለት መከፈል የጀመረው ፓርቲ፤ እስር ቤት ሲገባ ለሦስት (እስር ቤት የገባው፣ እስር ቤት የገባው እና የአቶ ልደቱ)፣ ፓርላማ ውስጥ ለአራት (እስር ቤት የገባው፣ የአቶ ልደቱ፣ የአቶ አየለ ጫሚሶ እና የአቶ ተመስገን ዘውዴ)፣ እውቅናውን ለማግኘት ለአምስት (የአቶ ተመስገን ቡድን ለሁለት ሲሰነጠቅ - የአቶ ተመስገን እና የአቶ ዓሊ አበጋዝ ቡድን)፣ ከእስር ቤት በኋላ ለስድስት (የኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል ቡድን በአንድ ወገን፣ የእነ ወ/ት ብርቱካን እና የዶ/ር ብርሃኑ አንድ ላይ ሆነው በሌላ ወገን)፣ በመጨረሻም “አንድነት” እና “ግንቦት ሰባት ንቅናቄ” ላይ ልዩነቱ ሰባት ደርሷል።

 

በሀገር ውስጥ ያለው የመጨረሻው የሚመስለው የፓርቲው አባላት ክፍፍል፤

 

1ኛ) ዋናውን የቅንጅት ሠርተፍኬት የያዘው የእነ አቶ አየለ ጫሚሶ ቡድን፣

2ኛ) የእነ ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል ቡድን፣

3ኛ) የፓርላማ ቡድን (እነ አቶ ዓሊ አበጋዝ)፣

4ኛ) የተቀላቀሉት የአቶ ተመስገን ዘውዴ ቡድን እና የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ቡድን

5ኛ) የእነ አቶ ልደቱ ኢዴአፓ መድኅን ናቸው።

 

አንድነትን በመመስረት ሂደት ላይ ተሰብስበው የነበሩት የላዕላይ ም/ቤት አባላት

ቅንጅት ሕጋዊ ሠርተፍኬቱን ለማግኘት መርጦት ከነበረው 60 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ውስጥ “አንድነት” ፓርቲን ለመመስረት በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሯ ሰብሳቢነት 20 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ቀርተው ነበር። በእዚህ ቁጥር ላይም እነ አቶ ተመስገን ዘውዴን ጨምሮ 17 አዲስ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ተጨምረዋል።

 

ሰኔ ሰባት ቀን 2000 ዓ.ም. አንድነት ፓርቲን ለመመስረት የሚደረገው ምርጫ ምን ዓይነት ይዘት ሊኖረው ይችላል? ፓርቲው ሲመሰረትስ የትኞቹን የቀድሞ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ያካትታል? በሚል አስተያየቶችን ከምንጮቻችን አሰባስበናል።

 

ከ60ዎቹ የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባላት ውስጥ 20 አባላት አንድነት ፓርቲን ለመመስረት ተሰብስበው ነበር። እነኝህም የሚከተሉት ናቸው፦

 

1) ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣

2) ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው፣

3) አቶ አክሊሉ ግርግሬ፣

4) አቶ አስቻላቸው ከተማ፣

5) አቶ ዘለቀ ዓለሙ፣

6) ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣

7) አቶ ክፍሌ ጥግነህ፣

8) ዶ/ር ሚኪያስ አባይነህ፣

9) አቶ ታምራት ታረቀኝ፣

10) ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣

11) ወ/ሮ ላቀች ደገፉ፣

12) አቶ ሙሉጌታ ወንድም አገኝ፣

13) ዶ/ር ሽመልስ ተክለፃድቅ መኩሪያ፣

14) አቶ ዲባባ አመንሲሳ፣

15) አቶ የኔነህ ሙላት፣

16) አቶ አብዱ መንገሻ፣

17) አቶ ይላላ ተዘራ፣

18) አቶ ስለሺ ጠና፣

19) ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ እና

20) አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል።

 

አቶ ሙሉነህ ኢዩኤል እና ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ

የቅንጅቱ ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል “አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ”ን ለማቋቋም ሲደረጉ ከነበሩት ስብሰባዎች ላይ መቅረት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ጠቅላላ ጉባዔውን ለመጥራት ግንቦት 10 ቀን 2000 ዓ.ም. (ሜይ 18 ቀን 2008) በተደረገው ስብሰባ ላይ አልተገኙም።

 

ዶክተር በፍቃዱ ደግፌ በበኩላቸው፣ “አንድነት” የሚያካሂዳቸውን ስብሰባዎች መካፈል ካቆሙ ወራት መቆጠሩን እና ጠቅላላ ጉባዔውን ለመጥራት ግንቦት 10 በተደረገው ስብሰባ ላይ እሳቸውም አለመገኘታቸው ታውቋል።

 

ነገር ግን ዶክተር በፍቃዱም ሆነ አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል ከስብሰባ በመቅረት ተሳትፏቸውን አቋረጡ እንጂ እስካሁን ፓርቲውን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለድርጅቱ አለማስገባታቸው ታውቋል።

 

ከዚህ በኋላ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው

ቀሪዎቹ 18 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት አቶ መሐመድ ዓሊንና 17 ተጨማሪ አዲስ የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን ጨምረው ወደ አዲሱ ምርጫ ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

እነዚህ 36 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት እያንዳንዳቸው አራት፣ አራት ዕጩ ይዘው ይቀርባሉ፣ 144 የሚሆኑት ዕጩዎች ወደ 90 ዝቅ ተደርገው ለጠቅላላ ጉባዔ ይቀርባሉ።

 

ጠቅላላ ጉባዔው ከፈለገ 15 ዕጩዎችን በጥቆማ ይመርጥና 105 ያደርሳቸዋል፣ ከዚያም ምርጫ ያደርግና 75 ዕጩዎችን ያስቀራል።

 

እነዚህ 75 ዕጩዎች ተሰባስበው ምርጫ በማድረግ 15 ተጠባባቂ፣ 60 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ያደርሱታል።

 

የሥልጣን ክፍፍሉ ምን ሊመስል ይችላል?

 

በመጨረሻ የሚቀረው 60 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት፣ 18 የሥራ አስፈፃሚ አባላትን ይመርጣል። በአዲሱ አደረጃጀት አንድ ሊቀመንበር፣ አራት ምክትል ሊቀመንበርና አንድ ፀሐፊ ይኖሩታል። ይሄንን የሥልጣን ክፍፍል ተንተርሶ እነማን ሊቀመናብርት እና ፀሐፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ አራት ግምቶች ተሰጥተዋል። እነሱም፦

 

ግምት አንድ

ሊቀመንበር - ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፤

ምክትል ሊቀመናብርቶች - አቶ ተመስገን ዘውዴ እና ዶክተር ኃይሉ አርኣያ፣

ፀሐፊ - አቶ አሥራት ጣሴ

 

ግምት ሁለት

ሊቀመንበር - ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው፣

ምክትል ሊቀመናብርቶች - ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣

ፀሐፊ - ዶክተር ኃይሉ አርኣያ

 

ግምት ሦስት

ሊቀመንበር - ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም

 

ግምት አራት

ሊቀመንበር - ዶክተር ኃይሉ አርኣያ

 

ብዙዎች ወ/ት ብርቱካን በሊቀመንበርነት እንደሚመረጡ ያላቸውን ግምት ይገልጻሉ። ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ ወይዘሪቷ ገለልተኛ፣ የፓርቲውን ደንብና መመሪያ በማያወላውል ሁኔታ የሚያስፈጽሙ፣ በሰው ተፅዕኖ የማይመሩ፣ ለያዙለት ዓላማ ከልባቸው የቆሙ፣ ለስላሳ ባህሪ ቢኖራቸውም አመራራቸው ላይ ግን ጠንካራ እንደሆኑ ይገልጻሉ። በፓርቲው አካባቢ ያሉ ሰዎች ማን እንደሚመረጥ ሲያወሩ “ሴቷ” ብለው እንደሚሉ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

 

በመጨረሻም

 

ከምርጫው በኋላ የምርጫውን ውጤት፣ የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ፣ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና ማሟላት የሚገባቸውን ሰነዶች አሟልተው ለምርጫ ቦርድ ያስገባሉ። የፓርቲውን ሕጋዊ ሠርተፍኬት ማግኘት ያለማግኘት ጥያቄም በመጨረሻ በቦርዱ ውሳኔ እልባት ያገኛል።

 

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ምን ይላሉ?

 

ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ “ከዚህ በኋላ በተለይ ሀገር ቤት ተከፋፍለው እየተንቀሳቀሱ ባሉት ድርጅቶች ውስጥ የከፋና አስደንጋጭ ክፍፍል ሊከሰት አይችልም” ሲሉ ያላቸውን ግምት አስረድተዋል። አክለውም “አሁን በስተመጨረሻ ነገሮች እየጠሩና ግልጽ እየሆኑ መምጣታቸው ለሚደረገው ትግል ትልቅ ጠቀሜታ አለው” ብለዋል።

 

ይህንንም ሲያብራሩ “ከዚህ በኋላ ሁሉም ወገኖች ካለፈው ስህተታቸውና ጥንካሬያቸው ተምረው፣ ያዋጣናል በሚሉት መስመር በግልጽ ከተሰለፉ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ትግል የድርሻቸውን ለመወጣት ያስችላቸዋል” በማለት ለኢትዮጵያ ዛሬ አስረድተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ