”የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወጣትና ተተኪ ሯጮችን የማዘጋጀትና የማሰለፍ ብቃት ያንሰዋል” አትሌቲክስ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን

አትሌት ሙሐመድ ፋራህ በ10 ሺህ ሜትር የለንደን ኦሎምፒክ  ሲያሸንፍ Mohamed Farah of Great Britain crosses the line to win gold in the Men's 10,000m

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. August 4, 2012)፦ በዛሬው ዕለት በለንደን ኦሎምፒክ በተካሄደው የአስር ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ውስጥ የተወለደውና የ29 ዓመቱ የእንግሊዝ ሯጭ ሙሐመድ ፋራህ አንደኛ ሲወጣ፣ ኢትዮጵያውያኖቹ ወንድማቾች ታሪኩ በቀለ እና ቀነኒሳ በቀለ ሦስተኛና አራተኛ ወጥተዋል። ቀነኒሳ በቀለ በዚሁ ርቀት ያለፉትን ሁለት ኦሎምፒኮች ክብረወሰን መስበሩ ይታወሳል።

 

 

አትሌት ሙሐመድ ፋራህ በ10 ሺህ ሜትር የለንደን ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትነቱን አረጋግጦ የእንግሊዝን ባንዲራ ሲያውለበልብMohamed Farah of Great Britain celebrates winning gold in Men's 10,000m

ሙሐመድ ፋራህ ውድድሩን በ27፡30.42 ደቂቃ የጨረሰ ሲሆን፣ አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ደግሞ በ27፡30.90 ደቂቃ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ፣ ታሪኩ በቀለ በ27፡31.43 ደቂቃ ሦስተኛ በመውጣት የነኀስ ሜዳሊያ አግኝቷል። በዚሁ ርቀት ሁለት የኦሎምፒክ ክብረወሰኖችና የወርቅ ሜዳሊያ ያለው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን በ27፡32.44 ደቂቃ በመጨረስ አራተኛ ወጥቷል። አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረመድህን ደግሞ ውድድሩን በ27፡36.34 ደቂቃ በመጨረስ 8ኛ ወጥቷል።

 

ሙሐመድ ፋራህ ውድድሩን በቀዳሚነት ሲመራ Mohamed Farah leads the pack as he competes in Men's 10,000m Final

 

ኬንያዊው ቤዳን ካሪኦኪ ሙቺሪ 5ኛ፣ ኤርትራውያኑ ዘረሰናይ ታደሰ እና ተክለማሪያም መድህን 6ኛ እና 7ኛ፣ የቱርኩ አትሌት ፖላት ኬምቦይ አሪካን 9ኛ፣ እንዲሁም የኡጋንዳው አትሌት ሞሰስ ንኤማ ኪፕሲሮ 10ኛ ወጥተዋል። የአስር ሺህውን የወንዶች የሩጫ ውድድር አፍሪካውያኑ ተቆጣጥረውታል።

 

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

በዚህ ውድድር ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የኦሎምፒክ ክብረወሰን (27፡01.17) እና የዓለም ክብረወሰን (26፡17.53) በእጁ ይገኛል።

 

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እ.ኤ.አ. 2004 ግሪክ አቴንስ ላይ በተካሄደው የአስር ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር በ27፡05.10 ደቂቃ በመግባት የኦሎምፒክ ክብረወሰንን ሰብሮ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን፣ በዚያው በአቴንሱ ኦሎምፒክ በአምስት ሺህ ሜትር ውድድሩን በ13፡14.59 ደቂቃ በመጨረስ ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወሳል። በዚሁ ውድድር አትሌት ስለሺ ስህን ውድድሩን በ27፡09.39 ደቂቃ በሁለተኛ ደረጃነት በመፈፀም የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ አይቀነጋም።

 

እ.ኤ.አ. በ2008 በቤጂንጉ ኦሎምፒክ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የአስር ሺህ ሜትር ሩጫን በ27፡01.17 ደቂቃ በመጨረስ በ2004 (እ.ኤ.አ.) በራሱ የተይዞ የነበረውን የኦሎምፒክ ክብረወሰን ማሻሻሉ ይታወቃል። አትሌት ስለሺ ስህን ሁለተኛ፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ደግሞ ስድስተኛ በመውጣት ውድድሩን መጨረሳቸው ይታወሳል።

 

ከዚህም ሌላ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በተካሄደው የወንዶች 5 ሺህ ሜትር ለ24 ዓመታት በሞሮኮዋዊው ሰዒድ አዊታ ተይዞ የነበረውን የኦሎምፒክ ክብረወሰን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ አይዘነጋም። ቀነኒሳ የርቀቱን ክብረወሰን የሰበረው ውድድሩን በ12፡57.82 ደቂቃ በመጨረስ ነበር።

 

በ10 ሺህ ሜትር ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ታሪክ

በ10 ሺህ ሜትር ለመጀሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ማሞ ወልዴ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1968 ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ነበር ያገኘው። በ1972 እ.ኤ.አ. ምሩፅ ይፍጠር የነኀስ፣ በ1980 ምሩፅ ይፍጠር የወርቅ፣ መሐመድ ከድር የነኀስ፣ በ1992 አዲስ አበበ የነኀስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል።

 

ከእ.ኤ.አ. 1996 ጀምሮ እስከ አለፈው 2008 በተደረጉት አራት ኦሎምፒኮች ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ሁለት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት የሀገራቸውን ባንዲራ አውለብልበዋል።

 

አትሌት ኃይሌ እ.ኤ.አ. በ1996 እና በ2000 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሲያገኝ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ እ.ኤ.አ. በ2000 የነኀስ ሜዳሊያ አግኝቷል። እ.ኤ.አ. በ2004 እና 2008 አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ ሜዳሊያዎች ሲያገኝ፣ አትሌት ስለሺ ስህን ደግሞ በሁለቱም ኦሎምፒኮች የብር ሜዳሊያዎች አግኝቷል።

 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

ሀገር ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን የሚመርጠውና የሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤ በተደጋጋሚ ለውድድር የሚያሰልፋቸው የተወሰኑ አትሌቶችን በመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያ ልታጣቸው የማይገቡና ልታስከብራቸው የሚገቡ ውድድሮችን ስትሸነፍ መቆየቷ ይታወቃል። ይህ የለንደኑ የአስር ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫም ከነዚህ ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቷል።

 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተደጋጋሚ ከሚተችባቸው ሥራዎቹ አንዱ፤ ተተኪ አትሌቶችን ለማሰለፍ አለመቻሉ እንደሆነ የዚህ ውድድር ውጤት በቂ ምስክር እንደሆነ ውድድሩን የተመለከቱና ውጤቱን የሰሙ አትሌቲክስ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ይጠቁማሉ። ”የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወጣትና ተተኪ ሯጮችን የማዘጋጀትና የማሰለፍ ብቃት ያንሰዋል” በማለት ይተቻሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ