ለወጪ ቁጠባ ኢትዮጵያውን አትሌቶች በቤጂንጉ መክፈቻ አልተሳተፉም
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉበትን የጊዜ ሠሌዳና ስለኦሎምፒኩ መረጃዎች ይዘናል
Ethiopia Zare (እሁድ ነኀሴ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. August 10, 2008)፦ ዓርብ ነኀሴ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. (በፈረንጆች 080808) በቻይና ቤጂንግ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነሥርዓት ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያልተገኙ ሲሆን፣ የተገኙት አብዛኞቹ የኢህአዴግ ሰዎች መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ በመክፈቻው ሥነሥርዓት ላይ ያልተገኙት ለአየር መበከሉ ሲባል እና ለወጪ ቁጣባ በሚል ሰበብ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የጎረቤት ሀገር የሆነችው የኬንያ አትሌቶች ግን ሁሉም በዚሁ የመክፈቻ ስነሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
በስነሥርዓቱ ላይ ከተገኙት የኢህአዴግ ሰዎች ውስጥ ለሚሊኒየም ጽሕፈት ቤት የተሾመው አቶ ስዩም በረደድ መገኘቱ ታውቋል።
በ1972 ዓ.ም. የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኘው አትሌት ምሩጽ ይፍጠር በዚሁ የመክፈቻ ስነሥርዓት ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ዓርማ ያለበትን ባንዲራ ሲያውለበልብ የነበር። ባንዲራው ላይ ያለውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ዓርማ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደማይቀበሉትና ያላቸውን ተቃውሞ ሲገልጹ ተደምጠዋል።
በዚህ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ10,000 ሜትር፣ በ5,000 ሜትር፣ በማራቶን፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል እና በ1,500 ሜትር በወንዶችም በሴቶችም እንደሚሳተፉ መዘገባችን አይዘነጋም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸውን እነኝህን ውድድሮች ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድ የሚከተለውን የውድድር ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ አዘጋጅቶልዎታል። (ሰንጠረዡን ለማግኘት በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማግኘት እዚህ ይጫኑ!)
ስለቤጂንጉ ኦሎምፒክ ጥቂት ቁጥሮችና መረጃዎች
- 204 ሀገሮች በቤጂንጉ ኦሎምፒክ ተሳትፈዋል። በአቴንሱ 2004 እ.ኤ.አ. በተደረገው ኦሎምፒክ ይሳተፋሉ ተብለው የተጠበቁት 202 ሀገሮች የነበሩ ሲሆን፣ ጅቡቲ ሳትሳተፍ በመቅረትዋ 201 ሀገሮች ተሳትፈዋል። በአቴንሱ ኦሎምፒክ ከተሳተፉት ሌላ በቤጂንጉ የሚሳተፉት ሦስቱ ተጨማሪ ሀገሮች ውስጥ ጅቡቲ አንደኛዋ ስትሆን፣ ሁለተኛዋ ደግሞ ጁላይ 3 ቀን 2006 እ.ኤ.አ. ነፃነትዋን ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሪፑብሊክ የተቀናጀችው ሞንቴኔግሮ ነች። ሦስተኛዋ ሀገር ደግሞ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው የቱቫሉ ደሴቶችም ናት።
- 1,000,000 የውጭ ሀገር ሰዎች ኦሎምፒኩን ምክንያት በማድረግ ቤጂንግ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- 100,000 ፖሊሶችና የጥበቃ ኃይሎች ኦሎምፒኩን ምክንያት በማድረግ በቤጂንግ በጥበቃ ላይ ተሰማርተዋል
የመክፈቻ ስነሥርዓቱ
- 100 ሚሊዮን ዶላር ($) - ለመክፈቻ ስነሥርዓቱ የተገመተው ዝቅተኛ ወጪ ሲሆን፣ $ 476,000 በደቂቃ፣ $ 8,000 በሰከንድ ነው። የመክፈቻ ስነሥርዓቱ 4 ሰዓት ፈጅቷል። የቤጂንጉ ወጪ የአቴንሱን የ2004 እ.ኤ.አ. የመክፈቻ ወጪ እጥፍ ነው።
- 35,000 ሪችቶች በስታዲየሙ ተተኩሰዋል።
- 2,583 የመብራቶች ቁጥር ሲሆን፣ 6,440 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ፈጅቷል።
- ከ80 በላይ ሀገር መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አንዱ ናቸው።
አዲሱ የአየር ማረፊያ ተርሚናል 3
- 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አዲሱን የአየር ማረፊያ ተርሚናል 3’ን ለመገንባት የፈጀው ገንዘብ ሲሆን፣ 140 የእግር ኳስ ሜዳዎችን የሚያክል የ3 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው፣ 50,000 ሠራተኞች ለ4 ዓመታት በግንባታው ላይ ተሠማርተዋል። በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞች ይጠቀሙበታል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከፈንሣይ ህዝብ ቁጥር ጋር እኩል ነው።
የወፍ ጎጆ ቅርጽ ያለው የኦሎምፒኩ ስታዲየም (የመክፈቻ ስነሥርዓቱ የተካሄደበት)
- 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር (3.4 ቢሊዮን የን፣ 318 ሚሊዮን ዩሮ) ለግንባታው እንደፈጀ ይነገራል። የተገነባው ቤጂንግ ውስጥ ሲሆን፣ ልዩ ስሙ ”ኦሎምፒክ ግሪን” በሚባል ሥፍራ ነው። ለአትሌቲክስና ለእግር ኳስ የሚሆን ስታዲየም ሲሆን፣ ንብረትነቱ የህዝባዊ ሪፑብሊክ ቻይና መንግሥት ነው።
- 258,000 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ነው የተገነባው፣ 91,000 ተመልካቾችና መቀመጫዎች ነበሩት በመክፈቻው ስነሥርዓት ላይ ነበሩት። ለኦሎምፒኩ ተብሎ 11,000 ጊዜያዊ መቀመጫዎች የተጨመሩበት ሲሆን፣ ከኦሎምፒኩ በኋላ የመቀመጫዎቹ ቁጥር 80,000 ይሆናል፣
- 330 ሜትር ርዝመት፣ 220 ሜትር ስፋት፣ 69.2 ሜትር ቁመት አለው፣
- 36 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለውና 49,600 ቶን ክብደት ያለው ያልተቆረጠ ብረት የተሠራ ነው።
- 2004 እ.ኤ.አ. ግንባታው ተጀምሮ ማርች 2008 እ.ኤ.አ. ተጠናቅቋል።
888 "የዕድል ቁጥር"
- 16,400 ጥንዶች በትንሹ በቤጂንግ ብቻ በአውሮጳውያኑ 2008፣ ስምንተኛ ወር፣ ስምንተኛ ቀን (080808) ላይ ተጋብተዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በተለያዩ የቻይና ግዛቶች እንደተጋቡ ይገመታል። 080808 (ሦስት ስምንቶች) በበርካታ ቻይናውያን ዘንድ ዕደለኛ ቁጥርና ቀን ተደርጎ ይታመናል። እንዲህ ያሉ የቁጥር መግጠሞች በመቶ ዓመት አንዴ ነው የሚከሰተው። በተለያዩ የዓለም ክፍሎችም በዚሁ ዕለት ሺህዎች የሚቆጠሩ ጥንዶች እንደተጋቡ የተለያዩ የዓለም ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ከመክፈቻ ስነሥርዓቱ ጥቂት ቪዲዮዎችና ፎቶዎች
የሪችት ስነሥርዓቱ በከፊል
በፎቶና በሙዚቃ የተቀናበረ ቪዲዮ



