ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ቦክሰኛ ከኦሎምፒክ ውድድር ውጭ ተደረገ
Ethiopia Zare (እሁድ ነኀሴ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. August 10, 2008)፦ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በቦክስ ውድድር በብቸኝነት ያሰለፈችው ቦክሰኛ ሞላ ጌታቸው አምባው በክብደት ምክንያት ከውድድሩ መታገዱን ዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር አስታወቀ።
ቦክሰኛ ሞላ ጌታቸው ከአፍሪካ ለኦሎምፒክ ማጣሪያ በተደረገው የ51 ኪሎ ክብደት ውድድር ላይ ሦስተኛ በመውጣት የነኀስ ሜዳሊያ አግኝቶ ለኦሎምፒክ አልፎ ነበር። ሞላ ጌታቸው የሚወዳደርበት ክብደት ከ49 - 51 ኪሎ ግራም እንደነበር ታውቋል።
ከሞላ ሌላ የእንግሊዙ የቀላል ሚዛን (59 - 61 ኪሎ) የዓለም ሻምፒዮና የሆነው ፍራንኪ ጋቪን እና ከ51 - 54 ኪሎ ደግሞ አሜሪካዊው ጋሪ ሩሴል የሚወዳደሩበትን ክብደት ባለማሟላታቸው ምክንያት ከውድድሩ ሊወጡ መቻላቸው ታውቋል።
ከ77 ሀገራት የሚካፈሉት 283 ቦክሰኞች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ 29ኙ ከአፍሪካ ሀገራት መሆናቸው ታውቋል።



