የ5 ሺውን የሴቶች ማጣሪያ ሦስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አለፉ
ቅዳሜ የሚደረገው ፍፃሜ በጉጉት ይጠበቃል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ነኀሴ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. August 19, 2008)፦ ዛሬ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በሁለት ምድብ በተደረገው የሴቶች 5,000 ሜትር ማጣሪያ የተሳተፉት ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማጣሪያውን አለፉ።
ከምድብ አንድ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ውድድሩን በ15፡09.89 ደቂቃ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ አትሌት መሰለክ መልካሙ ደግሞ በ15፡11.21 ደቂቃ አራተኛ በመሆን ጨርሳለች። ከምድብ ሁለት አትሌት መሰረት ደፋር ማጣሪያውን ያለፈችው በ14፡56.32 ደቂቃ በአንደኝነት ሲሆን፣ በማጣሪያው የተሻለ ሰዓት አስመዝግባለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቤጂንጉ ኦሎምፒክ የሚሳተፉትን አትሌቶች ይፋ ባደረገበት ወቅት በ5,000 ሜትር የሴቶች ሩጫ ይሳተፋሉ ካላቸው አራቱ አትሌቶች ውስጥ አትሌት በላይነሽ ፍቃዱ በዚህ የማጣሪያ ውድድር ያልተሳተፈች ሲሆን፣ ምክንያቱ አንድ ሀገር በአንድ ውድድር ላይ ከሦስት አትሌቶች በላይ ማሳተፍ ስለማትችል እንደሆነ ለመረዳት ችለናል።
የፊታችን ዓርብ ነኀሴ 16 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 22, 2008) በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ለአስር ሰዓት ሃይ ጉዳይ (3፡40 P.M. / 15፡40) ላይ ሲሆን፣ በተለይ በኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ መሠረት ደፋር እና ጥሩነሽ ዲባባ መሃከል ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖር ስለተገመተ ውድድሩ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
በዚህ ርቀት የዓለም ክብረወሰን ያለው በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ኦስሎ ኖርዌይ ላይ ያስመዘገበቸው 14:11.15 ደቂቃ ነው። የኦሎምፒክ ክብረወሰን ደግሞ በሩማኒያዊቷ ጋብረኤላ ዛቡ ስድኒ አውስትራሊያ ላይ የተመዘገበው 14:40.79 ደቂቃ ነው።
የወንዶች 5,000 ሜትር ማጣሪያ ነገ ረቡዕ ነኀሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 20, 2008) በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት ከሩብ (3፡15 P.M. / 15፡15) ጀምሮ በሦስት ምድቦች ይካሄዳል። በዚህ ርቀት የሚሳተፉት አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ አብርሃም ጨርቆሴ እና ዓሊ አብዶሽ ናቸው።
የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል
ትናንት ሰኞ ነኀሴ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. በተደረገው የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ በብቸኝነት አልፎ የነበረው ያዕቆብ ጃርሶ ውድድሩን በ8፡13.47 ደቂቃ በመግባት አራተኛ የወጣ ሲሆን፣ ኬንያዊው ብሪሚነ ኪፕሮፐ ኪፕሩቶ በ8፡10.34 ደቂቃ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
ፈረንሣዊው ማህዲን ሜኺሲ ሁለተኛ የወጣው ውድድሩን በ8፡10.49 ደቂቃ በመግባት የብር ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን፣ ኬንያዊው ሪቻርድ ኪፕኬመቦይ ማቴሎንግ ደግሞ በ8፡11.01 ደቂቃ ሦስተኛ ወጥቶ የነኀስ ሜዳሊያ አግኝቷል።
የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረወሰን 7፡53.63 ደቂቃ ሲሆን፣ ሴፕቴምበር 3 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. ብራስልስ - ቤልጅየም ላይ ኳታራዊው ሳይፍ ሰዒድ ሻኸን ያስመዘገበው ነው። የኦሎምፒኩ ክብረወሰን ደግሞ 8፡05.51 ደቂቃ ሴኦል - ኮሪያ ላይ ሴፕቴምበር 30 ቀን 1988 እ.ኤ.አ. በኬንያዊው ጁልየስ ካሪኡኪ የተመዘገበው ነው። (ቀሪዎቹን ውድድሮች ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድና ቀሪዎቹን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድር ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድ ያዘጋጀነውን የውድድሩን የጊዜ ሠሌዳ እዚህ በመጫን ያገኙታል!)



