(ተጨማሪ ዘገባ የታከለበት)

ወደ ሆስፒታሎች የተወሰዱትና ክፉኛ የቆሰሉቱ ለሕይወታቸው ያሰጋቸዋል

DS tvEthiopia Zare (ረቡዕ ነኀሴ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. September 03, 2008)፦ አውቶቡስ ተራ አካባቢ መናኸሪያ ሊደርስ ትንሽ ሲቀረው የዲ.ኤስ. ቲቪ ኳስ ማሳያ ቤት ውስጥ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ (በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር) በተከሰተ ከፍተኛ ፍንዳታ እስካሁን አራት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ሃያ አንድ የሚደርሱ ሰዎች መቁሰላቸውና በተለያዩ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን በሆስፒታል አካባቢ ሁኔታውን የሚከታተል የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጭ ጠቆመ።

 

እንደታማኝ ምንጫችን ክትትል ለአውቶቡስ መናኸሪያው በጣም ቅርብ በሆነውና በአካባቢው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚካሄድበት ቦታ በተነሳው ፍንዳታ የቆሰሉ ሰዎች ጥቁር አንበሳ፣ ራስ ደስታ፣ የካቲት 12  እና ጳውሎስ ሆስፒታሎች የተወሰዱ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ በተዘገበበት ሰዓት አንድ አስከሬን ከራስ ደስታ ሆስፒታል ሲወጣ መታየቱን የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል።

 

ፍንዳታው የተከሰተው መናኸሪያ አካባቢ በሚገኘው በዲ.ኤስ. ቲቪ የፕሪምየር ሊግ እግር ኳስ በሚታይበት ቤት ውስጥ ሲሆን፣ በወቅቱ የፕሪምየር ኃይላቶች እየታዩባት በነበረበት ሰዓት ነው። በፍንዳታው ሕይወታቸውን ያጡትና ክፉኛ የቆሰሉትና የተጎዱት ግን ከቤቱ ውጭ በአካባቢው የነበሩት መሆናቸው ታውቋል።

 

ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት 25 ሰዎች ውስጥ እስከ ምሽቱ ድረስ በሕይወት የተረፉት ሃያ አንዱ ሲሆኑ፣ ከእነሱም ውስጥ አስጊ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንዳሉ ለመረዳት ችለናል።

 

በአካባቢው የሚገኙ ሱቆችና የተለያዩ የንግድ ቤቶች በፍንዳታው የተጎዱ ሲሆን፣ ሠራተኞቹም ለከፍተኛ መቁሰል አደጋ መዳረጋው ታውቋል።

 

ፍንዳታው የፈንጂ መሆኑን ምስክሮች የተናገሩ ሲሆን፣ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ስለሁኔታው የተገለጸ ነገር የለም።

 

ዲ.ኤስ. ቲቪ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ፕሪምየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በቀጥታ ለመመልከት የሚያስችለውን የቴሌቭዥን ካርድ የሚሸጥ ድርጅት ሲሆን፣ በርካቶች በየሦስት ወሩ የሚታደሰውን ካርድ በመግዛት የማሳያ ቦታዎችን እያዘጋጁ እያስከፈሉ ያሳያሉ። የዛሬው ፍንዳታ የተከሰተበት ቤት ከዲ.ኤስ. ቲቪ የቴሌቭዥን ካርድ ገዝቶ ለደንበኞቹ እያሳየ በነበረ ቤት ውስጥ ነው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ