የመናኸሪያው ፍንዳታ የስምንት ሰው ሕይወት ቀጠፈ
ከምርጫ 97 ወዲህ በተከሰቱ 13 ፍንዳታዎች 36 ሰዎች ሲሞቱ ወደ 200 ሰዎች ቆስለዋል
(ሪፖርታዥ)
Ethiopia Zare (እሁድ ጳጉሜን 2 ቀን 2000 ዓ.ም. September 07, 2008)፦ በአዲስ አበባ በአውቶቡስ ተራ አካባቢ "መናኸሪያ" ሊደርስ ትንሽ ሲቀረው በተከሰተው አሰቃቂ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቅጥር ስምንት የደረሰ ሲሆን፣ በሃያ አራት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል። አሰቃቂውን ፍንዳታ በሚመለከት ዝርዝር ዘገባ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።
ለአራት ዓመታት ወደሠራችበት ፎቶ ቤት ስታመራ ከወትሮው የተለየ ችግር ይገጥመኛል ብላ ያላሰበችው የ20 ዓመቷ ወጣት ሃና ጎሣዬ (በፎቶግራፉ ላይ የምትታየው)፣ ከመኖሪያ ቤቷ አቅራቢያ ወደሚገኘውና ለሀገር አቀፍ መናኸሪያ (አውቶቡስ ተራ) የተጠጋውና መርካቶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሥራ ቦታዋ “ፎቶ ሻርፕ” የሄደችው በእግሯ ነበር።
ባለፈው ረቡዕ ቀኑን ሙሉ ሥራ መዋሏን የገለፁት ባልደረቦቿና የዓይን እማኞች፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ በተሰማው ከፍተኛ ፍንዳታ በኋላ በድንገት ተመትታ ወደቀች።
“የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ናት፣ ከተወለደችበት ሻሸመኔ ከተማ በሦስት ዓመቷ መጥታ በአያቷ እጅ ነው ያደገችው። ሥራ ከተቀጠረች በኋላ በምታገኘው ደመወዝ ራሷን እያስተዳደረች፣ ትምህርቷንም እየተማረች ነበር የምትኖረው …” ሲሉ እህቷና ወንድሟ ሲቃ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።
መኖሪያ ቤታቸው ፍንዳታው በደረሰበት አካባቢ በመሆኑና ከፍተኛ የሆነ የፍንዳታ ድምፅ ሰምተው ወደ ቦታው ሲሄዱ፣ እህታቸው መመታቷና በጣም በመጎዳቷ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መወሰዷ ይነገራቸዋል። ወደዚያ ሲያመሩ ግን የሃና ሕይወት በማለፉ ለአስከሬን ምርመራ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል መወሰዱ ተነግሯቸዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 62 የመርካቶን ክልል በመጨረስ፣ ወደ አዲስ ከተማ ት/ቤት መዳረሻ አካባቢ ቀኙን ይዘው የተደረደሩ፤ ሊያ ጁስ ቤት፣ ኮከብ ሙዚቃ ቤት፣ ሙሉብር ባርና ሬስቶራንት፣ አምባሰል ሙዚቃ ቤት፣ አምባሰል ልብስ ስፌት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ... የተባሉ በርካታ ሱቆች አሉ። በእነዚህ ሱቆች ግራና ቀኝ በሚገኙት ፎቶ ሻርፕ እና በዕድገት ኤሌክትሮኒክስ መሀል ለመሀል በፍንዳታው ደብዛው ከመጥፋቱ በፊት “አብዱ ሶከር ዲኤስ ቲቪ” የሚል የእግር ኳስ ማሳያ ቤት ነበር።
አቶ አብዱልአዚዝ አብዱል ከሪም ከባለቤቱ ጋር መኖሪያ ቤታቸውንና የዲ.ኤስ. ቲቪ ማሳያ ቤቱን ከፋፍለው ራሳቸውን ያስተዳድራሉ። ረቡዕ ዕለት ማለትም ነኀሴ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. ከአክስትና የአጎት ልጆቻቸው ጋር በአጠቃላይ ስድስት ዘመዳሞች ስብስብ ብለው ተቀምጠው ይጨዋወታሉ። በማሳያው ክፍልም በዕለቱ የሚተላለፍ ጨዋታ ባለመኖሩ ዲ.ኤስ. ቲቪ የሚያዘጋጀውን የኳስ ጨዋታዎች ቅንጭብጭብ (Highlights) ለማየት ወደ ማሳያው ቤት የገቡ ጥቂት ወጣቶች አሉ።
ከየት የመጣና ምን እንደሆነ ያልታወቀ ነገር በከፍተኛ ድምፅ መፈንዳቱንና ወዲያውኑ አካባቢው በአቧራ ጭስ መታፈኑን ይገልፃሉ። የተወሰኑ ተጎጂዎች በመስታወት ፍንጥርጣሪ ደም በደም ሲሆኑ፣ ወደ ላይ በማስፈንጠር ጣራ ላይ የተገኙም አሉ፣ ከብሎኬት የተሠሩ ፍርስራሾች የወደቀባቸውና ፍንዳታው የፈጠረው እሳት የለበለባቸው ተጎጂዎችም አሉ።
ወትሮውኑም በርካታ የሰዎች እንቅስቃሴ የማይጠፋበት ፍንዳታው የደረሰበት የአውቶቡስ ተራና የመርካቶ አካባቢ ወዲያውኑ በሰዎች ተሞላ።
ታክሲዎች የጫኑትን ሰው እያራገፉ፣ የቤት መኪናዎችንም የያዙ ተጎጂዎችን ወደ ሆስፒታል መውሰድ በጀመሩበት 10 ደቂቃ ውስጥ ፖሊስ አካባቢውን በቁጥጥር ስር በማድረጉ፣ የሆስፒታልና የፖሊስ አምቡላንሶች ተጎጂዎችን እየለቀሙ ወደ ራስ ደስታና ጳውሎስ ሆስፒታል መውሰድ ጀመሩ።
በመንገዱ መኪኖች እንዳያልፉ ከተደረገና ፍንዳታው የደረሰበት አካባቢ በፖሊስ ቢጫ ገመድ ታስሮ፣ ሰዎች እንዳያልፉ ከተከለከሉ በኋላ በርካታ ፖሊሶች ተጨማሪ ተጎጂዎችንና አካባቢውን መመርመር ጀመሩ።
ራስ ደስታ ሆስፒታልም ቤተሰቦቻቸውን በሚፈልጉ ሰዎች ዋይታና ትርምስ ተሞልቶ ነበር።
ራስ ደስታ ሆስፒታል ከተወሰዱት 13 ተጎጂዎች ውስጥ ሁለቱ ለአስቸኳይ ቀዶ ጥገና እንዲተኙ ሲደረግ፣ ሁለቱ ወደ ጥቁር አንበሳ፣ ሁለቱ ደግሞ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሪፈር ተደረጉ። ከስድስቱ ውስጥ አራቱ የዲ.ኤስ.ቲቪ ማሳያ ቤቱ ባለቤቶችና ዘመዶች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ሁለቱን ጨምሮ ጉዳታቸው በጣም ከባድ የሚባል ባለመሆኑ ድንገኛ ክፍል ባሉ አልጋዎች ላይ ተኝተው የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ ተደረገ።
በርካታ ፖሊሶችም ወደ ውስጥ ገብተው ምርመራ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ በጥቁር ላስቲክ የተጠቀለለ አስከሬን በቃሬዛ ይዘው ከድንገተኛ ክፍል ወጡ።
ሟቹ ማንነቱን የሚገልጽ ሰነድ በኪሱ ባለመኖሩ የሚያውቀው ቤተሰብ አልነበረውም። በፖሊስ የመኪና መብራት አማካኝነት ጥቁሩ ላስቲክ ተገልጦ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የታየው ይኸው አስከሬን ጠቆር ያለ ጅንስ ሱሪ፣ ውሃ ሰማያዊ ጅንስ ጃኬትና ነጭ ስኒከር የተጫማ ሲሆን፣ ከውስጥ ያደረገው ቲሸርት በደም የተለወሰ በመሆኑ ለመለየት ያስቸግራል። ይኸን የወጣት ገፅታ ያለውን አስከሬን፤ የተጎዳ ሰው ፍለጋ የመጣ አንድም የሚያውቀው ሰው ባለመገኘቱ “ሚስተር ዲ” የሚል ኮድ ተሰጥቶት አስከሬኑ በፖሊስ መኪና ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ተሸኘ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መግቢያ በር ላይ በወቅቱ ከጠፋው መብራት ጋር የቤተሰብ ፈላጊዎች ትርምስ ተጨማሪ ሰቆቃ ሆኖ ነበር። ወደ ሆስፒታሉ ውስጥ ሲገባ በርካታ መርማሪ ፖሊሶች ተጎጂዎችን ያነጋግራሉ፣ የሕክምና ባለሙያዎቹም ወደዚህና ወደዚያ ይራወጣሉ። በደም የተለወሱ የተጎጂዎች ልብስ በረንዳው ላይ ተከምሮ ይታያል። ወደ ሆስፒታሉ ከገቡት 15 ተጎጂዎች ሃናን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ በመሞታቸው አስከሬናቸው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ተወስዷል።
ሁለት ተጎጂዎች ጥቁር አንበሳ ሪፈር ሲባሉ፣ ሁለቱ ወደ የካቲት ሆስፒታል ተወስደዋል፣ ሁለቱ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል የተመሩ ሲሆን፣ ሦስቱ ቀዶ ጥገና ያስፈልግ አያስፈልጋቸው እንደሆነ ለመወሰን፣ ከመጀመሪያ ዕርዳታ በኋላ ምርመራ እየተደረገላቸው ቆይተዋል። የተቀሩት ጉዳታቸው ቀላል በመሆኑ የመጀመሪያ ዕርዳታ ተሰጥቷቸዋል። ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ፖሊሶችና ተረኛ ሐኪሞች ተነጋግረው የሞቱትን፣ ያሉትንና ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር የተባሉትን በመለየት ለፈላጊ ቤተሰቦች ካሳዩ በኋላ በር ላይ ተሰብስቦ የነበረውን ሰው በትነዋል።
አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ ፖሊሶች ምርመራ ሲያደርጉ ያደሩና የዋሉ ሲሆን፣ ኀሙስ ዕለት ከጠዋቱ 4 ሰዓት አካባቢ ማንነቱ ሊታወቅ በማይችልት ሁኔታ አንድ የተበላሸ አስከሬን ከፍንዳታው ቦታ ተገኝቷል፤ በመሆኑም የሟቾች ቁጥር ስምንት ደርሷል።
የፖሊስ መረጃም እንደሚጠቁመው 17 ወንዶች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ሁለት ሴቶች፣ አምስት ወንዶች በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ቀላል የሚባል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ስምንት ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ከቆሰሉት 24 ሰዎች ስድስቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ።
ከምርጫ 97 ወዲህ ባለፉት ሦስት ዓመታት በደረሱ ወደ 13 የሚጠጉ ፍንዳታዎች ወደ 36 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። በዚህ ዓመት በናሽናል ኦይል ኩባንያ እና በሚኒባስ ታክሲ ላይ የደረሱትን አሰቃቂ ፍንዳታዎች ጨምሮ በአዲስ አበባ፣ በሑመራና በጅጅጋ፣ ... ፍንዳታዎች መከሰታቸው አይዘነጋም።



