Wollega University

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም ከታኅሣሥ 20 ቀን ጀምሮ ትምህርት ተቋርጧል

ኢዛ (ማክሰኞ ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 31, 2019)፦ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት እስከ ረቡዕ ታኅሣሥ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙ ከኾነ ዩኒቨርሲቲውን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ ተገለጸ። ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም ከትናንት ታኅሣሥ 20 ቀን ጀምሮ ትምህርት ተቋርጧል።

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ለአራት ሳምንታት የተቋረጠውን የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሒደት ማስጀመር ባለመቻሉና እንዲህ ባለው ሁኔታ መቀጠል አስቸጋሪ በመኾኑ ነው።

በዚሁ መሠረት ትናንት ታኅሣሥ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ሴኔቱ ለተማሪዎቹ እንዳስታወቀው ትምህርቱን ለማስጀመር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ትምህርት ለማስጀመር ያደረገው ጥረት ሊሳካ ባለመቻሉ፤ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ሊወስን ችሏል። ተማሪዎች ፎርም በመሙላትና የሚመለከታቸውን ቢሮ ኃላፊ በማስፈረም፤ እንዲሁም በእጃቸው ያለውን የዩኒቨርሲቲውን ንብረት በመመለስ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የደረሰበትን ውሳኔ ለማስፈጸምም ይመለከታቸዋል ላላቸው አካላት አሳውቋል።

ይኸው የሴኔቱ ማስታወቂያ ትምህርት እየተከታተሉ ካሉ ተማሪዎች ውጭ ዩኒቨርሲቲው የሚሠጠውን ማንኛውንም አገልግሎት የሚያቋርጥ መኾኑንም አስታውቋል። የመልሶ ቅበላን በተመለከተም ወደፊት እንደሚያሳውቅም ገልጿል።

በተመሳሳይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከታኅሣሥ 20 ቀን ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት የተቋረጠ መኾኑ ተገልጿል። ይህንኑ በማስመልከት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በማስታወቂያ እንደገለጸው ከታኅሣሥ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊጀመር የነበረው ትምህርት ባጋጠመው ወቅታዊ ችግር በዩኒቨርሲቲው ትምህርት የማስቀጠል ሁኔታ አለመኖሩን አስታውቋል።

በመኾኑም ከትናንት ታኅሣሥ 20 ቀን ጀምሮ የመማር ማስተማሩ ሒደት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ወስኗል። ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎም ከታኅሣሥ 20 ቀን በኋላ ዩኒቨርሲቲው ምንም ዐይነት አገልግሎት የማይሠጥና ተማሪዎችን መልሶ የመቀበያ ጊዜም ወደፊት አስታውቃለሁ ብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ