የሞጣ ቃጠሎ

በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ የተሠራጨው በሞጣ የነበረው ቃጠሎ ከሚያሳይ ቪዲዮ ላይ የተወሰደ

የታሰሩት “በሞጣ የደረሰውን ውድመት መቆጣጠር እየቻሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም” በሚል ነው

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 2, 2020)፦ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰውና በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በመስጅዶች፣ ቤተክርስቲያንና በተለያዩ የንግድ ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል የተጠረጠሩ የሥራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ እንዳስታወቀው ለሦስት መስጅዶች፣ በአንድ ቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ባሉ ንግድ መደብሮች ላይ የደረሰውን ጥቃትና የንብረት ውድመት መቆጣጠር እየቻሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት አልቻሉም በሚል ነው የሥራ ኃላፊዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ከምሥራቅ ጐጃም ዞን የሞጣ ከተማ አስተዳደር የወጣው መረጃ፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የፖሊስ ወንጀል መከላከል ኃላፊ፣ የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የሚሊሻ ስምሪት ኃላፊ መኾናቸውን ይጠቅሳል።

እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች በወቅቱ ተገቢውን ሥምሪት ሠጥተው መከላከል በማድረግ ሁኔታውን መቆጣጠር እየቻሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ተጠርጥረው ስለመታሠራቸውን መረጃው ያመለክታል።

በሞጣ ከተከሰተው ጥቃት ጋር በተያያዘ 33 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውና ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መኾኑ መገለጹ አይዘነጋም። ከተያዙት ተጠርጣሪዎች ውስጥ በጣቢያ ቃላቸውን ገና ያልሠጡ ተጠርጣሪዎች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።

በሦስቱ መስጅዶች፣ በአንድ ቤተክርስቲያንና በንግድ ድርጅቶች ላይ የቃጠሎ አደጋው የደረሰው ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ መኾኑን መዘገባችን አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ