የቀድሞ የኢሕአዴግ ንብረትን ለማጣራት ኦዲተሮች ተሾሙ
ሕወሓት፣ ብልጽግና ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሕወሓትና ብልጽግና አንድ የጋራ አጣሪ መምረጥ አልቻሉም
ኢዛ (ቅዳሜ ሰኔ ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 13, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀድሞው የኢሕአዴግ ንብረት ክፍፍልን የቀረበለትን ጥያቄ ለመመለስ የግንባሩን ንብረት የሚያጣሩ ሁለት ኦዲተሮችን መሾሙን አስታወቀ።
ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በብልጽግና ስር ያሉ ሦስቱ ፓርቲዎችና ሕወሓት የኢሕአዴግ የመፍረስ ውሳኔ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙበት አንድ የጋር አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ነው።
ስለኾነው ሕወሓትና ብልጽግና ፓርቲ በየበኩላቸው የመረጡዋቸው አንድ አንድ የሒሳብ አጣሪዎች በጋራ በመኾን የንብረት ማጣራት ሥራውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ ሊያሳልፍ ችሏል። ቦርዱ በዚህ ላይ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ኢሕአዴግ እንዲፈርስ እንዲሁም የቀድሞ ሦስቱ የግንባሩ አባላት ወራሽ የኾነው ብልጽግና ፓርቲ እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በስድስት ወር ውስጥ የንብረት ክፍፍል ተጠናቆ እንዲያቀርቡ ክፍፍሉም የሦስት ፓርቲዎች ወራሽ የኾነው ብልጽግና የሀብቱን ሦስት አራተኛ (3/4) በራሱ ሕጋዊ እውቅና ያለው ሕወሓት አንድ አራተኛ (¼) እንዲወስዱ መወሰኑ ይታወሳል። በውሳኔውም ፓርቲዎቹ የጋራ ንብረት አጣሪ ሾመው የባለመብቶችን (creditors) መብት እንዲጠበቅ፤ እንዲሁም በተገለጸው ቀመር መሠረትም የንብረት ክፍፍሉ እንዲፈጸም ወስኖ አሳውቆ ነበር።
በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ እንጂ በእኩልነት ሊሆን አይገባም የሚል አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን፤ ቦርዱ የሀብት ክፍፍሉን የወሰነው የፓርቲው ሕገደንብ፤ “ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው” ሲል ያስቀመጠውን መሠረት በማድረግ መኾኑን ገልጾ፤ ኾኖም ግን ብልጽግና ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል ተገልጾለታል።
የመፍረስ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙበት አንድ የጋራ አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ስለኾነም ቦርዱ ብልጽግና ፓርቲ እና ሕወሓት በየበኩላቸው የመረጧቸው አንድ አንድ የሒሳብ አጣሪዎች በጋራ በመኾን የንብረት ማጣራት ሥራውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም ውሳኔ መሠረት የንብረት ማጣራቱን እንዲያደርጉ የተመረጡት ድርጅቶች የጋራ የሥራ እቅድ፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ ሥራውን የሚያከናውኑበት ቦታ፣ ሁኔታ እና የሥራ ሕግጋት ለቦርዱ እንዲያቀርቡም በደብዳቤ ተገልጾላቸዋል። የንብረት ማጣራቱ ሒደት ሙሉ ወጪ በፓርቲዎቹ የሚሸፈን ሲሆን፤ ቦርዱ ሒደቱ የሚደርስበትን ደረጃ በየጊዜው ለሕዝብ የሚያሳውቅ ይኾናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ



