ዓቃቤ ሕግ በእነአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ በ14 ቀን ክስ እንዲመሠርት ብይን ተሰጠ

አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (መኻል) እና አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ (በቀኝ)
በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በእነ አቶ እስክንድር ላይ እስከ ጳጉሜን 5 ድረስ ክስ እንደሚመሠርት ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ
ኢዛ (ሰኞ ጳጉሜን ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 7, 2020)፦ አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አስር ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ እስከ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ክስ እንዲመሠርት ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት (ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም.) ብይን ሰጠ።
አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለን ጨምሮ እስከ 10ኛ ተራ ቁጥር ያሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ እስከ መስከረም ክስ እንዲመሠርት ከሰጠው ብይን ሌላ፤ በዚሁ መዝገብ 11ኛ እና 14ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ ደግሞ በአምስት ቀን ውስጥ ክስ እንዲመሠርትም ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፤ በዋስትና ጥያቄው ላይ ትእዛዝ ሳይሰጥ ተጠርጣሪዎቹ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትእዛዝ ስለመስጠቱም ተዘግቧል።
የፌዴራሉ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ወንጀልን በሽምግልና የምንፈታበት ሕግም ሥልጣንም የለንም፤ በአደባባይ ሰው የገደሉንና ውድመት እንዲፈጠር ያደረጉ ተጠርጣሪዎችን ሳንመረምር አናስርም የሚል የለም፤ ማስረጃውንም መዝኖ ለሕግ የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዚሁ መግለጫቸው ላይ ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ግድያውን በመፈጸምና ግድያውን ተከትሎ በተፈጠረው ኹከት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ክስ የሚመሠረት መኾኑን ገልጸዋል። አያይዘውም በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ እንዲሁም በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የተከፈቱ መዝገቦች ላይ እስከ የፊታችን ሐሙስ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ክስ እንደሚመሠረት ሳይገልጹ አላለፉም። (ኢዛ)