Demeke Mekonen

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነዋሪው ትጥቅ መታጠቅ አለበት አሉ

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 12, 2020)፦ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪ ራሱን አደራጅቶ አስፈላጊውን ትጥቅ ታጥቆ የተጠናከረ መከላከል መገንባት አማራጭ የሌለው መኾኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። በዞኑ ትናንት ሌሊት 12 ንጹኀን ተገድለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ትናንት ሌሊት በዞኑ በንጹኀን ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በመተከል ዞን ከሚመራው ኮማንድ ፖስት አመራሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው።

በዞኑ እየተፈጸመ ያለው ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር የዜጎችን ሕይወት መጥፋት አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ ክስተት መኾኑን በመግለጽ፤ ድርጊቱን ስለመኮነናቸውም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረጃ ገጽ ላይ ሰፍሯል።

ወንጀለኞችን እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት የጠቀሱ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪን በተመለከተ ግን ነዋሪው አስፈላጊውን ትጥቅ ታጥቆ መከላከል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለመኾኑ አመልክተዋል።

ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር የሚታይበት የመተከል ዞን የንጹኀን ሕይወት እየጠፋበት ሲሆን፤ ትናንት ሌሊት በግለሰቦች መካከል ተፈጠረ በተባለ ግጭት የ12 ንጹኀን ዜጎች ሕይወት አልፏል። አቶ ደመቀም ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. አስተላለፉ የተባለው መልእክት ይህንኑ ድርጊት ተንተርሰው ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ