Lidetu Ayalew

አቶ ልደቱ አያሌው

የቢሾፍቱ ፖሊስ ትእዛዙን ባይፈጽም አዛዡ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀ
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ማብራሪያ እንዲሰጥ ታዟል

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 19, 2020)፦ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው ባስቸኳይ እንዲለቀቁና ይህ የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የማይፈጸም ከኾነ አቶ ልደቱን ይዞ በቆየው የቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀ። የኦሮሚያ ፖሊስም አቶ ልደቱ ታስረው እንዲቆዩ ያደረገበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ይህንን ትእዛዝ የሰጠው ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ነው። የዛሬው ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበረው የቢሾፍቱ ፖሊስ አቶ ልደቱ ፍርድ ቤቱ በወሰነላቸው ዋስትና መሠረት ለምን እንዳልለቀቃቸው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ነበር።

በዚሁ መሠረት ኃላፊው ፍርድ ቤት ቀርበው ስለጉዳዩ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ መልስ የሰጡ ሲሆን፤ በዚህ ምላሻቸው ለቦታው አዲስ ስለመኾናቸውና ጉዳዩን በደንብ የማያውቁ መኾኑን፤ እንዲሁም አቶ ልደቱ በሌላ ክስ የተከሰሱ በመኾናቸው ከመርማሪው ተረድቻለሁ፤ በቀጣዩ ቀጠሮ ስለጉዳዩ በደንብ አስረዳለሁ ማለታቸውም ተገልጿል።

ስለአቶ ልደቱ በእስር ያቆዩበትን ምክንያት በተመለከተ ከፖሊስ መምሪያ ኃላፊው የተሰጠውን ማብራሪያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ፤ ፖሊስ አቶ ልደቱን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ይህንን የፍርድ ቤት ትእዛዝ የማያፈጽሙ ከኾነ ግን፤ በፖሊስ አዛዡ ላይ እርምጃ የሚወሰድ መኾኑንም አስታውቋል።

በዛሬው ዕለት አቶ ልደቱ በአስቸኳይ ይፈቱ የሚለው ትእዛዝ ስለመፈጸሙ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቁም ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ዛሬ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የሰጠበትን ደብዳቤ ለፖሊስ መምሪያው እንዲደርስ የተደረገ ሲሆን፤ አቶ ልደቱን አስሯል የተባለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ለፍርድ ቤቱ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀርቦ እንዲያስረዳም ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላልፏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ