Lidetu Ayalew

አቶ ልደቱ አያሌው

ከልባቸው ሕመም ጋር በተያያዘ የተገጠመላቸው ሰው ሠራሽ መሣሪያን በተመለከተ የሕክምና ቀጠሯቸው በማለፉ ለሕይወታቸው አስጊ መኾኑን ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አሳውቀዋል

ኢዛ (ዓርብ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 30, 2020)፦ አቶ ልደቱ አያሌው ከተከሰሱበት ሁለተኛ መዝገብ ጋር በተያያዘ፤ ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው በዚህ መዝገብ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ የተቀረጸው ድምፅ ግልባጭ ከመዝገቡ ጋር ባለመያያዙ፤ የክስ መቃወሚያና ዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምሥራቅ ምድብ ወንጀል ችሎት፤ ይህንን ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው በሁለተኛው መዝገብ ሕገ መንግሥቱን ለማፍረስ በማሰብ የሽግግር ሰነድ ማዘጋጀት ክስ ላይ የዋስትና ጥያቄውንና የክስ መቃወሚያው ላይ ብይን ለመስጠት ቢኾንም፤ በዛሬው ቀጠሮ የዋስትና ጥያቄው ድምፅ ግልባጭ ባለመቅረቡ ነው።

አቶ ልደቱ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ የተቀረጸው ድምፅ ግልባጭ ያልቀረበው፤ የድምፅ ግልባጭ ባለሙያው እረፍት በመውጣታቸው ዛሬ ከመዝገቡ ጋር ሊቀርብ ባለመቻሉ ነው ተብሏል።

በዚህም ምክንያት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ የያዘበትን የዋስትና ጉዳይም ኾነ፤ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክርክሩ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር ባለመያያዙ በተለዋጭ ቀጠሮ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል። በተለዋጭ ቀጠሮው ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውንና በመጀመሪያ ደረጃ የመከራከሪያ መቃወሚያ ላይ ብይን ይሰጣል ተብሏል።

አቶ ልደቱ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ በመያዝ በተከሰሱበት መዝገብ በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ፤ እስካሁን ተግባራዊ ሳይኾን ቆይቷል።

አቶ ልደቱ አሁን ያሉበት ወቅታዊ የጤና ሁኔታ ሕክምና ካላገኙ አስጊ መኮኑን የሚያመለክት የሕክምና ማስረጃ ባለፈው ዓርብ ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አቅርበው እንደነበርም ታውቋል።

በዚህ የሕክምና ማስረጃ አቤቱታቸው ውስጥ ከዚህ ቀደም በተደረገላቸው የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና፤ የተገጠመላቸው ሰው ሠራሽ መሣሪያን በተመለከተ የሕክምና ቀጠሯቸው ማለፉ ለሕይወታቸው አስጊ በመኾኑ፤ ዋስትናው ተፈቅዶላቸው ታክመው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ነው።

በዚህ ዋስትና ጥያቄ ላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ልደቱ በዋስትና ወጥተው ወደ ውጭ ቢሔዱ፤ በዚያው ይቀራሉ በሚል ተቃውሞት እንደነበር አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ