በአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ተለዋጭ ቀጠሮዎች ተሰጡ
አቶ ልደቱ አያሌው (ፎቶ፡ ሪፖርተር)
የጤና ሁኔታቸው አስጊ ደረጃ ላይ መኾኑን በማመልከት ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ለኅዳር 18 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ
ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 5, 2020)፦ አቶ ልደቱ አያሌው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት በተከሰሱበት ወንጀል መከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ።
በዚህ መሠረት ፍርድ ቤቱ አቶ ልደቱ በተከሰሱበት ወንጀል ዓቃቤ ሕግ ያሰማቸውን ምስክሮች መከላከል የሚያስችል የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው እንዲያቀርቡ የሰጠውን ብይን ለመስማት ለኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ልደቱ በተከሰሱበት ሌላ መዝገብም በተመሳሳይ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። ይህም ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለማፍረስ በማሰብ የሽግግር መንግሥት ሰነድ ማዘጋጀት ወንጀል ክስ ነው። በዚህ የክስ መዝገብ የጤና ሁኔታቸው አስጊ ደረጃ ላይ መኾኑን በማመልከት ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮው የተሰጠው ለኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው። (ኢዛ)



