በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት አባላት ሕንፃዎች በገለልተኛ አካላት እንዲተዳደሩ ተወሰነ
በገለልተኛ አካል እንዲተዳደሩ ከተወሰነባቸው የጥቂቱ የሕወሓት አባላት ሕንጻዎች
ኮሜርሻል ኖሚኒስና የቤቶች ኮርፖሬሽን ሕንፃዎቹን ያስተዳድራሉ
የጀኔራል ፃድቃንና የጀኔራል ታደሰ ሕንፃዎች ይገኙበታል
ኢዛ (ዓርብ ሰኔ ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 25, 2021)፦ በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ዋና ዋና አባላት የንግድ እና የመኖሪያ ሕንፃዎች ላይ ገለልተኛ አስተዳዳሪ እንዲሾም ውሳኔ ተላለፈ።
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው በተለያዩ መዝገቦች ጉዳዩን ይዞ የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ሕንፃዎቹን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር የሚገኘው ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃ.የተ.የግል ማኅበር እንዲያስተዳድረው ውሳኔ መስጠቱንም ጠቅሷል።
እነዚህ ውሳኔ የተሰጠባቸው የንግድ እና የመኖሪያ ሕንፃዎች ቁጥር 30 ናቸው። ከእነዚህ ሕንፃዎች መካከል የቀድሞ ኤታማዥር ሹም ፃድቃን ገብረትንሳይ ስም የተመዘገቡ ሁለት ሕንፃዎች ይገኙበታል።
በብርጋዴር ጀኔራል ታደሰ ወረደ፣ በጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት፣ በብ/ጀኔራል ተክላይ አሸብርና በሌሎች የሕወሓት ቡድን አባላት የተመዘገቡ በአዲስ አበባና በመቀሌ የሚገኙ ሕንፃዎችም በገለልተኛ አስተዳዳሪው ተይዘው እንዲተዳደሩ ወስኗል። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ ይፋ ያደረገው ሙሉ መረጃ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሕወሓት የሽብር ቡድን አባላት ሕንጻዎች በገለልተኛ አስተዳዳሪ ተይዘው እንዲተዳደሩ ወሰነ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተለያዩ የመዝገብ ቁጥሮች (በመ/ቁ 007198፣ 263719፣ 007109፣ 006060፣ 263591፣ 006914፣ 006059 እና 007029) ሰኔ 16፣ 17 እና 18 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዋና ዋና የሕወሓት የሽብር ቡድን አባላት የንግድና የመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ገለልተኛ አስተዳዳሪ እንዲሾም ውሳኔ ሰጠ።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራል የኾኑት አቶ ዓምአንተ አግደው እንደገለጹት፤ ፍ/ቤቱ ይህንን ውሳኔ የሰጠው የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የወንጀል ምርመራና የሀብት ጥናት እየተከናወነ መኾኑን መነሻ በማድረግ፤ ቡድኑ ከሕንጻዎቹ የሚያገኘውን ገቢ የሽብር ተግባሩን ፋይናንስ ለማድረግ እንዳያውል ለመከላከል፣ በተጠረጠሩበት የሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች በፍ/ቤት ጥፋተኛ ኾነው ከተገኙ ሀብታቸው የሚወረስ በመኾኑ ተጠብቆ እንዲቆይ፣ የሽብር ቡድኑ በመከላከያ የሰሜን ዕዝ ሀብት፤ በተለያዩ መሠረተ ልማቶችና ሲቪል ተቋማት ላይ ላደረሰው ውድመትና ጉዳት ለማካካሻነት የሚውል በመኾኑ፣ እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን ንብረት የያዙ አካላት የሚፈጽሙትን ምዝበራ ለመከላከል ሲባል በተጠረጠሩበትና በተከሰሱበት ወንጀል ፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ገለልተኛ አካል እንዲያስተዳድራቸው ዓቃቤ ሕግ ለፍ/ቤት አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ነው ብለዋል።
ፍ/ቤቱ የዓቃቤ ሕግን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ሕንጻዎችን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር የሚገኘው ኮመርሺያል ኖሚኒስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር እንዲያስተዳድር ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህ ውሳኔ አስተዳዳሪ የተሾመላቸው የንግድና መኖሪያ ሕንጻዎች አጠቃላይ ብዛት ከ 30 በላይ ሲኾኑ ከእነዚህ መካከል፡-
በጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ስም አዲስ አበባ የሚገኙ 2 (ሁለት ሕንጻዎች) ፣
በጄ/ል አበበ ተክለሃይኖት ስም አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ G+5 ሕንጻ (ወለላ ሕንጻ)፣
በብ/ጄ ምግበ ኃያለ ስም አዲስ አበባ እና መቀሌ የሚገኙ 2 (ሁለት) ሕንጻዎች፣
በብ/ጄ ታደሰ ወረደ ስም መቀሌ የሚገኙ 2 (ሁለት) ሕንጻዎች፣
በብ/ጄ ተክላይ አሸብር ስም አዲስ አበባ የሚገኝ G+5 ሕንጻ (ብሌን ሕንጻ)
በብ/ጄ ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ ስም መቀሌ የሚገኙ 3 (ሦስት) ሕንጻዎች፣
በሜ/ጄ ሕንጻ ወ/ጊዮርጊስ ስም መቀሌ የሚገኝ 1 (አንድ) ሕንጻ፣
በሜ/ጄኔራል ኢብራሂም አብዱል ጄሊል ስም መቀሌ የሚገኝ 1 (አንድ) ሕንጻ እና
በኃይለ ተስፋኪሮስ ገ/ሕይወት ስም መቀሌ የሚገኙ 3 (ሦስት) የነዳጅ ማደያዎች ይገኙበታል።
በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አክለው እንደገለጹት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከዚህ በተጨማሪ በዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ እና የሜ/ጄ ጻድቃን ባለቤት በወ/ሮ ኤልሳ አሰፋ ተክለሚካኤል ስም የሚገኙ ሕንጻዎችን ጨምሮ በሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ሀብት ላይ አስተዳዳሪ ለማሾም እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በሀብት ምርመራ እና መለዬት ሒደት የሽብር ቡድኑ አባላት ተሽከርካሪዎችን ከቆሙበት በማንሳት ጋራዥ ውስጥ የመደበቅና አካላቸውን ፈቶ የማስቀመጥ፣ ለውጭ ዜጎች በማከራየት የኪራይ ገንዘብ ውጭ አገር ለመቀበልና በማሸሽ ለሽብር ዓላማ ለማዋል፣ የኪራይ ውሎችን በመንደር ውል በማድረግ ግብር እንዲሰወርና የሽብር ቡድን አባላትን ንብረት በኪራይ መያዛቸው እንዳይታወቅ የማድረግ ተግባር መፈጸም፣ አንዳንድ ሕንጻዎችን ለሌላ ሦስተኛ ወገን የባንክ ማስያዣ በማድረግ ገንዘብ የማሸሽ ሙከራዎች ስለማድረጋቸው ተረጋግጧል።
እነዚህን የወንጀሎች ተግባራትን አዲስ አበባ በሚገኙ ወኪሎችና ተከራዮች አማካኝት እየፈጸሙ መኾኑ በመታወቁ ከዚህ አንጻር ተጨማሪ ምርመራዎች በመጣራት ላይ ናቸው።
በመጨረሻም የሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት፤ የሕወሓት የሽብር ቡድን አባላትን ንብረት በኪራይ፣ በውክልና፣ በጠባቂነት፣ በአደራና በሌላ ማናቸውም መንገድ ይዘው የሚገኙ አካላት ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሕንጻ 1ኛ ፎቅ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ቢሮ በአካል በመቅረብ ወይም በስልክ ቁጥር 0112733154 ወይም በEmail፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በማሳወቅ ራሳቸውን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ እንዲያደርጉ፣
በሌላ በኩል ባንኮች ለሚሰጡት ብድር መያዣ የሚያደርጉት ንብረት የሕወሓት የሽብር ቡድን አባላት አለመኾኑን ወይም ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የሌለው መኾኑን አስቀድመው በቂ ማጣራት በማድረግ ማረጋገጥ ያለባቸው ሲሆን፤ ይህንንም ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ከሌሎች የሚመለከታው የሕግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በቅርበት መረጃ መለዋወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።



