ታላቅ ድል በቤጂንግ (ከአብርሃም ሰሎሞን)
ታላቅ ድል በቤጂንግ
አብርሃም ሰሎሞን ነኀሴ ፲፰ ቀን ፳፻ ዓ.ም. (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ስምሽ በዓለም ታውቋል ኮራን ሀገራችን፣
አላሳፈሩንም ጀግኖች ልጆቻችን።
የጀግኖች እናት ነሽ ለዘለዓለም ኑሪ፣
እናት ኢትዮጵያ በልጆችሽ ኩሪ።
ጀግና ልጆች ናቸው በድል የጠገቡ፣
ወርቅ፣ ብር፣ ነኀስ ካልያዙ የማይገቡ።
በሰገነቱ ላይ ለሽልማት ቆመው፣
የኢትዮጵያን የክብሯን መዝሙር አዘምረው።
ከፍ ብሎ ታይቶ ሰንደቅ ዓላማቸው፣
ዓለም አጨብጭቦ ለጀግንነታቸው፣
ያኔ ነው የሚገቡት ሀገር አስጠርተው፣
በደረታቸው ላይ ሜዳሊያ ደርድረው፣
ከአገር ይወጡና ባንዲራ ጨብጠው፣
በድል ይገባሉ ሜዳሊያ ጨምረው።
ግብርን አከናውኖ ድል አርጎ በብቃት፣
ባህል ሆኖ ቀረ ተሸልሞ መምጣት።
በስፔን ባርሴሎና በአትላንታ ሜክሲኮ፣
በሮም በቶክዮ በሲድኒ በሞስኮ፣
በግሪክ በቤጂንግ በኦሎምፒክ ሀገር፣
ይወራል ይሰማል የዝናቸው ነገር።
ዓለምን ድል አርገው በድል እየገቡ፣
በክብር መዝገብ ላይ ስም ያስመዘገቡ፣
ብዙ ልጆች አሉሽ በዝና የሚጠሩ፣
ሰንደቅ ዓላማሽን በውል ያስከበሩ።
ጀግና ልጅ አፈራሽ ዘንድሮም ይገርማል፣
ሮጦ የማይደክመው "ቀነኒሳ" የሚባል።
ከፍ አለ ባንዲራሽ ወደ ላይ ተነሳ፣
ለድል በመብቃቱ ጀግናው ቀነኒሳ።
አቴንስ የነበረው ውጤት ተደገመ፣
ቀነኒሳ ቤጂንግ ወርቅ ተሸለመ።
አዲስ ክብረ ወሰን ተገኘ ተጻፈ፣
ሽንፈት የማያውቅ ልጅ ዛሬም አሸነፈ።
ኢትዮጵያ ልጆችሽ ስምሽን ሲያስጠሩ፣
በኦሎምፒክ ሜዳ ሀገር ሲያስከብሩ፣
ለአሸናፊው ሲሰጥ ቀርቦ ሽልማቱ፣
ያለወርቅ አይለብሱም በየአራት ዓመቱ።
አበበ ጀምሮት ያውም በባዶ እግሩ፣
ወርቅ ይዞ ሲገባ ልዩ ነበር ክብሩ።
ዓለም እስከ ዛሬ ኦሎምፒክ ሲጀመር፣
ሳይተርክ አያልፍም የአበበን ድል ነገር።
የዛሬ ሃምሳ ዓመት በሮም ያሳለፈው፣
የዘላለም ታሪክ የዘላለም ስም ነው።
ሳይስማማው ቢቀር የቀረበው ጫማ፣
ባዶ እግሩን ዘለቀው የሮምን ከተማ።
ጫማ ምን ያደርጋል አብሮ አልተፈጠረ፣
ነካው በባዶ እግሩ ማርሽ እየቀየረ።
ያኔ ተጀመረ ድል በማድረግ ተድላ፣
ማራቶን ሲያሸንፍ አበበ ቢቂላ።
በኦሎምፒክ ሜዳ ድል ሲያደርግ አበበ፣
በአፍሪካ አዲስ ምዕራፍ ታየ ተዘገበ።
ሁልጊዜ ማሸነፍ ሁሌ አንደኛ መውጣት፣
ኦሎምፒክ ይመስክር ለሀገራችን ኩራት።
ጀግና በየዓመቱ እንደ እህል ሲመረት፣
ኃይሌ ቀነኒሳ ጥሩነሽ መሠረት፣
መዝገቡ ሲከፈት በውል የተጻፈው፣
የዓለም ክብረ ወሰን በእጃቸው ነው ያለው።
የረጅም ርቀት ድል ያደረግንበት የታወቅንበትን፣
አምስት ሺ፤ አሥር ሺ ደግሞም ማራቶንን፣
በእጃችን አርገናል ይኸው ለዘመናት፣
በኢትዮጵያ ልጆች ብቃትና ብርታት።
ስለ ሩጫ ነገር ሲታሰብ ሲታለም፣
ኃይሌ የሚባል ጀግና ትዝታ ነው ለዓለም።
ጭንቅ ነው ጥብ ነው በየሩጫው ሜዳ፣
ለመሮጥ ሲዘጋጅ ኃይሌ ሲሰናዳ።
ሯጭ ተሰልፎ ሩጫ ሳይጀምር፣
ወርቁ ለኃይሌ ነው እንዲህ ያለ ክብር።
በአትላንታ በሲድኒ ወርቅ የለመደ አንገት፣
በሁለት ኦሎምፒክ የታየው ጀግንነት፣
ዛሬ በአንተ ባይሆን በአንተ ላይ ባይሠራ፣
መውለብለቡ አልቀረም የኢትዮጵያ ባንዲራ።
አበበ ቢቂላ ሰምተኻል ወይ ጉዱን፣
ቀነኒሳ የሚባል ጀግና መወለዱን፣
ተምዘግዝጎ ሲበር ኃይል እየጨመረ፣
በምድር ላይ የሚበር ይመስል ነበረ።
ዓለም አስከትሎ ፊት ቀድሞ ሲገባ፣
ቤጂንግን ሲያደምቃት ሆታና ጭብጨባ፣
ድምፅ አልሰማህም ወይ ካንቀላፋህበት?
ሙት ይቀሰቅሳል የነበረው ጩኸት።
ክቡር ቀነኒሳ ከጀግናም ጀግና ነህ፣
እንኳን የሀገርህ ህዝብ ዓለም ያከበረህ።
ደወሉ ሲደወል ፍጥነት እየጨመርክ፣
ላይደረስብህ ላትያዝ አመለጥክ።
አንተን ተከትለው እንቀድማለን ላሉት፣
የኅልም ሩጫ ሆነ ከኋላ ለቀሩት።
አንተ የድል ሰው ነህ ወደፊት ሄደኻል፣
እግርህ ላይ ክንፍ አለ ላትያዝ በረኻል።
እንደ ምሩፅ ይፍጠር እንደ ሀገርህ ጀግና፣
ሁለት ወርቅ አግኘተህ ተሞላህ በዝና።
ዛሬም እንደ ትናንት እንዳለፈው ዘመን፣
ኦሎምፒክን ፈጸምክ በአዲስ ክብረወሰን።
ከግምት ያለፈ ከአዕምሮአችን በላይ፣
ዓለም ያስደመመው የጥሩነሽ ጉዳይ፣
በአምስት ሺ በአስር ሺ በረጅም ርቀት፣
ሁለት ወርቅ ያገኘ በቀናት ልዩነት፣
እስከ ዛሬ ድረስ የለም አልነበረም፣
ድል የሰመረለት ድል የቀናው በዓለም።
ከጀግናም ጀግና ነሽ ምድርሽን ያስከበርሽ፣
አዲስ ክብረወሰን በዓለም ያስመዘገብሽ።
በምን ቃል እንጥራሽ ምን ስያሜ እንስጥሽ፣
"ጥሩነሽ" ብለውሽ እናትና አባትሽ።
የድሉን ምልክት መስመሩን ሳታልፊ፣
ገፅሽ ምስክር ነው እንድታሸንፊ።
አንድ ነው ቢባልም ይመሰላል በሺ፣
ሀገር አስከብሯል ጀግና ነው ስለሺ።
እንደ ወፍ የሚበር በሚያስገርም ፍጥነት፣
ኢትዮጵያ ውለጂ የስለሺን ዓይነት።
የወርቁን የብሩን የነኀሱን ሜዳሊያ፣
ያበረከታችሁ ለአንዲት ውድ ኢትዮጵያ፣
ስለሺ ጥሩነሽ ፀጋዬ መሠረት፣
ደግሞም ቀነኒሳ ሁላችሁ በአንድነት፣
ለመጪው ኦሎምፒክ ሌሎች ጨምራችሁ፣
ተዘጋጅታችሁ ኑ እግዚአብሔር ይርዳችሁ!
የኢትዮጵያ ልጆች ውድድር ጨርሰው፣
የወርቅ፤ የብር የነኀስ ሜዳሊያ ተጋርተው፣
አዲስ ክብረወሰን በዓለም አስመዝግበው፣
ቤጂንግን ሲለቁ ስንብት አድርገው፣
ድል እየታያቸው ለሚመጣው ዘመን፣
እንዲህ ነበር ያሉት የመጨረሻው ቀን፣
"ለዛሬ አራት ዓመት ለአዲስ ክብረወሰን፣
ደህና ሁኚ ቤጂንግ እንገናኝ ለንደን።"
ወ ስ ብ ሐ ት - ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
አብርሃም ሰሎሞን - ነኀሴ ፲፰ ቀን ፳፻ ዓ.ም.
(This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)