እህ ዛዲያማ! - ቅጽ ፪ (ከወለላዬ)
እህ ዛዲያማ! (ቅጽ ፪)
ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
እህ ዛዲያማ እህ ዛዲያማ
በአንድ ጎጆ አንድ ቁርንጮ ይነጠፍና እንድትናገር ይፈቀድና
በዛ ጎዳና ገፍተህ ስትሄድ
ብለው ይሉሃል ወሕኒ ቤት ውረድ
ምን ትላላችሁ ይሄንን ጉዳይ
ደኅናው ሲታሰር ተቀምጦ ገዳይ
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን ልበላችሁ
ሁሉንም ነገር ታውቁታላችሁ
ለዲሞክራሲ ላገር ነፃነት
በሙሉ አለብን አብረን መነሳት
ወድቀን አንወድቅም ይሄው በሩጫ
ወስደን ተመልሰን ያለምን ዋንጫ
ማንአለ እንደኛ የማይፈራ ሞት
የሚያንበረክክ ሳይተኩስ ጥይት
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን ልበላችሁ
ሁሉንም ነገር ታውቁታላችሁ
ምንም ቢገጥመን ጭንቅ መከራ
ተስፋ ሳንቆርጥ ጭራሽ ሳንፈራ
እናጠናክረው የትግሉን ጎራ
እንደኛ የለም ሞቶ እሚያሸንፍ
ታሪክ በደሙ ደጋግሞ እሚጽፍ
ምንም ቢያጠቁን ይዘውብን ቂም
እንነሳለን ወድቀን አንቀርም
ዘሬን ለይቼ አላውቅም ነበር
እሱው ነገረኝ እንዳለኝ ብሔር
ምን ያገባኛል እኔ በቃሉ
ኢትዮጵያዊነት ካለልኝ ውሉ
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን ልበላችሁ
ያለውን ጉዳይ ታውቁታላችሁ
ሳንከፋፈል በዘር በጎሣ
ከዳር እስከዳር በሉ እንነሳ
እንግዲህ ይብቃ መግለጫ ወሬ
እናሳይ በወግ የትግሉን ፍሬ
ካስር ንግግር ጥያቄና መልስ
ይሻላል ቆርጦ የልብን ማድረስ
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን ልበላችሁ
ሁሉንም ነገር ታውቁታላችሁ
ብዬ ብላቸው ኑሮ ከበደኝ
የኢኮኖሚ ዕድገት ነው አሉኝ
በኢኮኖሚ መሻሻል ዕድገት
ሀገር በረሃብ አለቀ በሞት
ደግሞ እሚገርመው የእግዜሩ ነገር
የሱ አይደለም ወይ ያበሻ ምድር
ያንን አትበሉ እሱ አለው መንገድ
ኃያል ነው ክንዱ ሲቀጣ ሲያወርድ
ተዋርዶ ኑሮ ተዋርዶ መሞት
አንገሽግሾናል በቅቶናል በሉት
እስከመቼ ነው እያልን ዋይ ዋይ
ከነሱ ጋራ አብረን ምንቆይ
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን አጣላችሁ
አብሮ እንደማበር በጠላታችሁ
ምኑ ሊጠቅም ሥልጣን ፍለጋ
ሁሉ ወጥቶበት ለተንቋቋ አልጋ
ባረባ ነገር መፋጀት ትተን
የህዝብን ጠላት እንጣል ጎትተን
ካዘጋጁልን የጥፋት ወጥመድ
መዳን አለብን ዘጋግተን መንገድ
ያፍሪካ መሪ ሲያገኝ ሽልማት
ያፍሪካ መሪ ሲያበዛ ሹመት
መድረሱ አይቀርም አስደንጋጭ ውርደት
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን ልበላችሁ
ይጠንክር ያብብ አንድነታችሁ
በያለንበት ሠላም እናውርድ
በፀብ ጥላቻ ትግሉን አንናድ
ይበቃል በዚህ በሉ አታስጩሁኝ
ለሌሎች መንገር መሄድ አለብኝ
ጧፉን አንድደን ለኩሰን ሻማ
መዳን እንቻል ከዚህ ጭለማ
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ ምን ልበላችሁ
ዓመቱን የድል ያድርግላችሁ!
ጤናና ፍቅር ሠላም ይስጥችሁ!
ወለላዬ (ከስዊድን) መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም.
September 25, 2008 - Sweden