በድል እንግባ! (ከወለላዬ)
በድል እንግባ!
ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
(ግጥሙን ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)
በመጥፎ አገዛዝ ሀገር ሲታመስ፣
በደልና ግፍ ህዝብ ላይ ሲደርስ።
በዲሞክራሲ በፍትህ እጦት፣
ሰዉን በረሃብ ሲቀጡት በሞት።
ምን ትሠራለህ እዚህ ተቀምጠህ፣
ከጀግኖች አብር ውጣ ተነስተህ።
እያለኝ ልቤ መንፈሴ ሮጦ፣
አካሌን ሳየው እዚህ ተቀምጦ።
ያሳፍረኛል መቆም መኖሬ፣
ቁጭ ማለቴ ነፍሴን ቋጥሬ።
አዎን! አፍራለሁ ስሟን ስሰማ፣
ሳልላት ስቀር ”አይዞሽ እማማ!”።
”እሪ! በይ አለኝ ሂጂ ብረሪ”፣
ስትል ሰማሁኝ ያገሬ አዝማሪ።
እኔም ይለኛል ሂድ ብረር ብረር፣
ዛሬ ማምሻህን ወተህ እዛ እደር።
ጥፋተኞችን ሰብስበህ ቅጣ፣
ሀገርህን አድን ህዝቡን ነፃ አውጣ።
ረሃብ አጥፋ ፍርድን አስተካክል፣
እውቀት ጉልበትክን ላገርህ አውል።
እረስ ሰንጥቀህ ያገርክን ሜዳ፣
እሾኩን ንቀል አረሙን አጽዳ።
ሀገርህ ገብተህ በቋንቋህ አውራ፣
ጠላቷን ጥለህ ሸልል አቅራራ።
ተነስ ጨክነህ ጉብዝናህ ይታይ፣
ምን ትሠራለህ ሂድ አንተ ኮብላይ።
ጅብ ከሚበላህ በልተህ ተቀደስ፣
ውለህ አትደር ተነሳ ገስግስ።
እስከመቼ ነው የምትወሸቅ፣
ሀገርህን አድን ተነሳ ታጠቅ።
ዛሬ ነው አንተ የልጅነትክን፣
በችግሯ ቀን መርዳት እናትክን።
ሲደላትማ ስታገኝ ነዋይ፣
ፈረንጅም ሄዶ ይሞቃል ፀሐይ።
ምንም አይጠቅምም ”ሀገሬ!” - ”ሀገሬ!”፣
እዚህ ተቀምጠህ ብትጠርቅ ወሬ።
ውለህ አትደር ይልቅ ተነሳ፣
ሀገር ገጥሟታል ትልቅ አበሳ።
አለዛ ሀገሬ ስትለማማ፣
ይስቅብሃል ጎንደር ሲሰማ።
ቅኔ ብትቀኝ ብትጽፍ ግጥም፣
ምንም አይጠቅመው ዛሬ ለጎጃም።
ይልቅ ተነሳ እግርህ ይዘርጋ፣
እየጠራህ ነው ድፍን ወለጋ።
በግልጽ ይታወቅ ድጋፍህ ላገር፣
አለሁኝ በለው ሂድ ኢሉባቡር።
በዛው አቋርጠህ ገብተህ ከከፋ፣
በጠዋት ዘልቀህ እጎሙጎፋ፣
በዳይዋን ቅጣ ጠላቷን አጥፋ።
እረፋዱ ላይ ማምሻህን ደግሞ፣
እድፏን አጽዳ ወርደህ ሲዳሞ።
መቼም አይተኛ የሀገር ሎሌ፣
ችግሯን ቅረፍ ግባና ባሌ።
አጥፊዋን አባር ከሀገር ምድር፣
ቁም ነገር ሥራ ዘልቀህ ከሐረር።
እንዳይበግርህ ስንፍና አታሎ፣
ሰንኮፏን ንቀል ጎራ በል ወሎ።
በሰሜን በኩል ግባና ትግራይ፣
ህዝቡን አላቀው ከነፍሰ ገዳይ።
አርሲ ወርደህ ሄደህ አሰላ፣
ሀገሩን አጽዳ ከወሮበላ።
ሸዋን አላቀህ ከወንበዴ እጅ፣
እኩልነትን ሠላምን አውጅ።
ያዋረዷትን ያገር ባንዲራ፣
ከፍታ ቦታ ሰቅለህ ተራራ።
ስለነፃነት ከስሩ ዘምር፣
ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ሠላምን አብስር።
መከፋፈልን በዘር በጎሣ፣
አዋጅ ደንግገህ ካገርህ አንሣ።
እያለ ልቤ ተነስቷል የኔ፣
ምን ታስባበህ አንተስ ወገኔ?
ከኔ ጋር አብር ተነሳ ታጠቅ፣
ለዚህ ተልዕኮ አብረን እንዝለቅ።
ውለን ሳናድር ሄደን በአንድነት፣
ሁሉን ፈጽመን በያለንበት።
እመሀል ሀገር አዲስ አበባ፣
እንሰባሰብ በድል እንግባ!
ወለላዬ (ከስዊድን) መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም.
October 6, 2008 - Sweden