የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ (ከወለላዬ)
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
ከወለላዬ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
(ግጥሙን ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
ሆነ ነገሩ ተቀያየረ
ኑጉ ነጣና ወተት ጠቆረ
ፀሐይ አበራች ከታች ወደላይ
ፈሪ ሆነ አሉ ጠላትን ገዳይ
መንገድ ሲመራ ሲያሳይ እውሩ
ዓይናሞች ዋሉ ሲደናበሩ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
እንደ ቲማቲም እንደ ሠላጣ
ድንች ይመስል ወይ እንደ ቆስጣ
እንደጤፍ እህል እንደ ማሽላ
እንደ ስንዴና እንደ ባቄላ
መሬትን ቆርሶ ቆሞ ቸርቻሪ
አገኘን ይሄው ነጋዴ መሪ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
አብረው ሸፍተው ባመጡት ጣጣ
መናወጥ ያዙ በህዝብ ቁጣ
ውል ተዋውሎ አያ ጅብ ከጅብ
አንዱ ተራበ አንዱ ሲጠግብ
መግቢያ እንዳያጣ መሄጃ ሥፍራ
አዋጁን ሊያሽር ሴናተር ጠራ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
ዓባይ እውጪ ማፍሰስ አቁሞ
ወደኛ መጣ አሸዋ ቅሞ
ዕድሜ ከስጠ ይደርሳል ተረት
ዝንቦቹ ከበው ንቡን ገደሉት
በንቀት አይቷት እያላት ችላ
ትልቁ ድመት ባይጥ ተበላ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
አትናገሩ አትጻፉ ብሎ
ጋዜጠኖችን እወህኒ ዶሎ
ላገር ለወገን ለህዝብ ያሰቡት
ኡ! ኡ! እያሉ ነው በፍትህ እጦት
የዛሬ ዳኛ እንዳሉት አድሮ
እንዴት ሰው ይፍታ እራሱ ታስሮ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
መንግሥት እራሱ ሆኖ ነጋዴ
ቀረጥ ሳይከፍል ከበረ ባንዴ
እራሱ ሸጦ እሱ እየገዛ
እንደቅቤ ቅል አናቱ ወዛ
ህዝብ ሳያየው ውጪ ሳይወጣ
በቴሌቪዥን የሚያዝ መጣ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
የማያስፈልግ እሳት አንድዶ
ሰባ ሺህ ወገን ጨረሰ ማግዶ
ለሱ እንዲስማማ ሕግ አንተርሶ
ምረት አረገ በሐሰት ከሶ
እኔ ነኝ አለ ባለቦላሌ
መንግሥት የሌለው ገድሎ ሶማሌ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
አይግጠው ነገር አይሆነው ዳቦ
መንገድ ሠራለት ህዝብ ተርቦ
ይለው ጀመረ ተስፋፍተህ ንዳ
እንኳን ጤፍና አጥቶ ዘንጋዳ
የራሱ አሮበት የሰው ሲያማስል
እጫፍ ላይ ደርሷል ሊገባ ገደል
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
እንዳይፈነዳ እንደ ቮልካኖ
እረግጦ ይዞ ህዝቡን አፍኖ
ተንቀጠቀጠ እላዩ ሆኖ
በሩጫ ሰበብ ሰዉ ቢወጣ
የጦር አዛዡ ፊቱ ገረጣ
የሚናገረው የሚለው ጠፋ
ብርቱ ምላሱ ሆነ ኮልታፋ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
ተመሰቃቅሎ መልኩን ለውጦ
ሎሚ ጣፈጠ ወይን ኮምጥጦ
መሆኑ ቀርቶ በወግ በማዕረግ
በር ተዘግቶ ተሰረገ ሠርግ
በዛሬው ውሎ እገበያ ላይ
ከወርቅ በልጦ ተሸጠ ድንጋይ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
ሆነ ነገሩ ተቀያየረ
ሌባ በተራው ዳኛን አሰረ
ፀሎቱን ትቶ ቆሞ መቀደስ
ተቀባይ ሆነ ዘፋኝን ጳጳስ
ላንድነት ብሎ ሲሞት ቴዎድሮስ
ከፋፍሎ ገዢ መጣልን ንጉሥ
የፈና ጅራ የፈና ጅርቱ
እናቷን አንቺ ልጅቷን አንቱ
ወለላዬ ከስዊድን መስከረም ፬ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
September 14, 2008 - Sweden