ድምፃችን ይሰማ!

ወለላዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

(PDF

በሙስና በማጭበርበር፣

በአፈና ሰው በማሰር፣

ሥልጣን ሹመት የያዛችሁ፣

የግፍ ጥርጊያ መንገዳችሁ፣

እጅግ ጠቧል ወዮላችሁ፣

በህዝብ ላይ እንደበፊት፣

ተነስታችሁ በአጉል እብሪት፣

እጃችሁን ብትዘረጉ፣

ዝም አንልም ልብ አድርጉ።

- ባራክ ኦባማ

 

ገና ከመነሻው ሥርዓት ለማስከበር፣

ታላቁ ኦባማ ይሄን ብለው ነበር።

ነገር ግን ወያኔ አሁንም ኢህአዲግ፣

በመብት ረገጣ ህዝብን በማስበርገግ፣

ሽብርን በመፍጠር በእስራት በአፈና፣

ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሀገር ነስቷል ጤና።

የቀድሞን ቅንጅት የአሁንን አንድነት፣

ሥርዓት አስይዘው ሲመሩ የቆዩት፣

ዳኛዋ ብርቱካን - ብርቱካን ሚደቅሳ፣

እየቆጠሩ ነው እስር ቤት አበሳ።

አንድነት ፍቅርን ሠላምን በመስበክ፣

“ኑ! እንተባበር” ስላለ በመድረክ፣

ሀገር ያደነቀው ወጣቱ ቴዲ አፍሮ፣

ዓመት ሊሞላው ነው ወህኒ ተወርውሮ።

እንዲሁም ብዙ ሰው በሰበብ አስባቡ፣

በእስር ቤት ሆኗል ኑሮና ቀለቡ፣

ሀገርን አድርገው እንደተራ ሸቀጥ፣

ቆራርጠው ዳር ዳሩን ጀምረዋል መሸጥ።

ስለዚህ ወተናል ይሄን በመቃወም፣

ስቃዩን በደሉን ይወቅልን ዓለም።

የአሜሪካን ግዛት ትልቁን ከተማ፣

በመምራት ላይ ላሉት ለባራክ ኦባማ፣

መልዕክታችን ይድረስ ድምፃችን ይሰማ!

እንዳሉትም ሁሉ እንደተናገሩት፣

ለመኖር እንዲችል ህዝብ በነፃነት፣

ካጋጠመው ችግር ድኖ እንዲተነፍስ፣

ትዕዛዝዎ ይምጣ ይላክ ከኋይት ሐውስ

ጠመንጃ ወድረው ሥልጣን የጨበጡ፣

ከግፍ ወንበራቸው ይውረዱ ይቀጡ።

ትልቅ ስፍራ እንዲይዝ ስምዎ በታሪክ፣

ይህን አጋጣሚ ይጠቀሙ ባራክ፣

ለአፍሪካ ጭቁን ህዝብ ለተተኪው ትውልድ፣

የነፃነት ድልድይ ይክፈቱለት መንገድ።

ማንም ካሁን ወዲያ በሥልጣን ላይ ወጥቶ፣

የግፍ ተንኮል አክሊል እራሱ ላይ ደፍቶ፣

ለመያዝ እንዳይችል ህዝብን አሰቃይቶ፣

የኃላፊነት ድርሻ ሥራዎ ነውና፣

ጉዳዩን አብጠርጥረው ይዩት በጥሞና።

ኢትዮጵያን የያዘው መንግሥትም እንዲወርድ፣

ዲሞክራሲ እንዲያብብ ጭቆና እንዲወገድ፣

በእስር እንዳይማቅቅ ህዝብ እንዳይሰደድ፣

ከጎናችን ቆመው ያመቻቹ መንገድ።

ይሄ መልዕክታችን ታላቁን ከተማ፣

በመምራት ላይ ላሉት ለባራክ ኦባማ፣

ዛሬውኑ ይድረስ ድምፃችን ይሰማ!!!

 


 

(በፍርድ መዛባት በየእስር ካምፑ አላግባብ ታጉረው ለሚገኙት ወገኖቻችን መታሰቢያ ይሁን።)

ወለላዬ ከስዊድን መጋቢት 2001 ዓ.ም.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ