ልዑል ሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ ሰብሳቢን ስለ ምርጫ አንዳንድ መረጃዎች ለመጠየቅ ከቢሯቸው በር ላይ እጠብቃለሁ። አቶ ከማል በድሪ የቦርዱ ሊቀመንበር፣ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባልም ናቸው። በተሰጣቸው ሥልጣን ከሳቸው በላይ ስለ ምርጫው ሊጠየቅ የሚገባው የለም ብዬ ነበር የግድ እሳቸውን ለማግኘት ደጅ የጠናሁት።

 

ሰዓቱ እየገፋ መሔድ ጀመረ። ተስፋ ሳልቆርጥ መጠበቄን ቀጠልኩ። ፀሐፊዎች ቢሯቸውን እየቆለፉ ወጥተዋል። በቦርዱ ካለው ቢሯቸው መግቢያ እኔና በርቀት ፈንጠር ብሎ የቆመው ጠባቂያቸው ብቻ ተፋጠናል። ወደ አቶ ከማል የላኩኝ በቅርቡ “ቦርዱ ነፃ ነው” የሚል ስብከት በአሜሪካ ድምፅ ሲሰጡ የሰማችኋቸው አቶ ተስፋዬ መንገሻ ናቸው።

 

በሀገራችን አቆጣጠር ከምሽቱ 12 ሰዓት ግድም እየሆነ ነው። የቦርዱ ግቢ ጭር ማለት ጀምሯል። ፀሐፊያቸው ሲወጡ ታናግራቸዋለህ ባትለኝና ጠባቂያቸውን ባላይ ኖሮ በዚያ ሰዓት ቢሮ ይኖራሉ ብዬ ባላመንኩ ነበር። ድንገት አንድ መኪና ከውጭ እየተንደረደረች ገብታ የአቶ ከማል ቢሮ ፊት ለፊት ቆመች። በሮች በፍጥነት ተበረገዱ። አቶ በረከት ስምዖን በግራ እጃቸው ወረቀቶች እንደያዙ ሰተት ብለው ገቡ። የቦርዱ ሊቀመንበር ከሥራ ሰዓት ውጭ ሲጠብቋቸው የነበሩት አለቃቸውን መሆኑ ገባኝ።

 

አቶ በረከት የወያኔ ምርጫ ኃላፊ ሲሆኑ፤ አቶ ከማል በድሪ ደግሞ ዛሬም ድረስ “ነፃ ነው” እየተባለ በወያኔ የሚጮህለት የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር። ሁለቱ ጠባቂዎች የሞቀ የትውውቅ ሠላምታ እንደጨረሱ ፈንጠር በል የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠኝ። በኋላ ከቦርዱ አካባቢ ባገኘሁት መረጃ ከስልክ ያለፈ መመሪያ ለቦርዱ ኃላፊዎች የሚሰጥበት የተመረጠ ሰዓት መሆኑን አወቅሁ።

 

ይሄ የሆነው በ1997 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዛሬም የዚህ ቦርድ ኃላፊዎች የወያኔ ጉዳይ ፈጻሚዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል። የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ታሪካዊ ነው ከሚሰኝባቸው ምክንያቶች መካከል ለእኔ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፍ/ቤት፣ የመከላከያ፣ የደህንነት እንዲሁም ፓርላማው ምን ያህል ነፃ አለመሆናቸው በወሬ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠበት ወቅት መሆኑ ጭምር ነው። ከዚህ በኋላ ነው ቢያንስ የውጭው ዓለምን ጨምሮ ብዙዎች በጭፍን ተቃዋሚዎችን ምርጫ ግቡ ከማለት አልፈው ተቋማቱ የግድ አስፈላጊዎች መሆናቸውን የተረዱት።

 

የምርጫ ቦርድ በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ከምርጫው በፊት የወያኔ እጩዎች ሲመረጡባቸው ያውቃል። ድምፅ ተቆጥሮ ሳያልቅ እነአቶ መለስ ከሕግና ሥርዓት ውጭ የህዝብ ድምፅ ዘርፈው “መንግሥት ለመመስረት የሚያበቃ ድምፅ አግኝተናል” ሲሉ ተቀብሎ ያንኑ እንደታዘዘው አድርጓል። የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎች ከየወረዳው ዞን ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይመጡ፣ ከመጡም እንዳይረከቡ ለኃላፊዎች ከወያኔ መሪዎች የተሰጠው ትዕዛዝ ወደታች የወረደው በእነ አቶ ተስፋዬ፣ በእነ አቶ ከማል በድሪ በኩል ነው።

 

ህዝቡ የሰጠው ድምፅ መከበር አለበት ብለው ድምፅ ቆጥረው ማረጋገጫ ፈጥነው የሰጡ አንዳንድ የምርጫ አስፈጻሚዎች መከራ አግኝቷቸዋል። በተቃራኒው የእነአቶ መለስን አፍ እየተከተሉ የህዝቡ ድምፅ ሲሰረቅ አብረው የሰረቁ በምርጫ ማጣራቱ ወቅት ከወያኔ ጎን በመሰለፍ ምርጫ ቦርድ ፍፁም አሻንጉሊት መሆኑን በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ጭምር ያሳዩ ታማኞች ተሹመዋል፤ ተሸልመዋል። በዚህ ብቃታቸው ለቀጣዩ ምርጫ መታጨታቸው አይቀርም።

 

የእነአቶ መለስ የአፈና ቡድን የመራጩን የህዝብ ድምፅ መስረቅ ብቻ ሳይሆን በዝረራ የተሸነፈባቸውን አካባቢዎች ሁሉ ተበቅሏል። ከየአካባቢው የተቃዋሚ ታዛቢዎችን፣ የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎችን፣ የምርጫ ቅስቀሳ አደረጉ ያላቸውን ሁሉ አስሯል፤ ገድሏል። ለአካል ጉዳት የተዳረጉትን ቤቱ ይቁጠራቸው።

 

ንጹኀን “ድምፃችን ይከበር!” ብለው ስለጮሁ ብቻ በእነአቶ መለስ ቁጥጥር ስር በተዋቀረው የአጋዚ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያና የክልል ፈጥኖ ደራሾች ደማቸው በከንቱ ፈሷል። ከ197 በላይ ንጹኀንን ያስገደሉት ለፍርድ አልቀረቡም ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ አካባቢዎች የታሰሩት ሰዎች ዛሬም አልተፈቱም።

 

ምርጫ ያለ ነፃ ተቋማት ማለትም ያለ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ፣ ያለ ነፃና ገለልተኛ የፖሊስ፣ የመከላከያ፣ የደህንነት ተቋማት፣ ያለ ነፃ ፓርላማ፣ ያለ ነፃ ፍርድ ቤት እና ያለ ነፃ ሚዲያ ዋጋ እንደሌለው ምርጫ 97 በተግባር አሳይቷል።

 

በህዝብ ድምፅ የተዘረሩት የምርጫው አሸናፊዎችን ጭምር ገለዋል። እነአቶ ጁነዲን ሳዶን ያሸነፉት የተቃዋሚ ተመራጭ ስለተመረጡ ብቻ ተገለዋል። በሻሸመኔ ዛሬ የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁ የተሸነፈበትን ወረቀት ለመቀየር የኦብኮ ተወካይ የምርጫው ምሽት ቆጠራው ላይ ተገድሏል። የዚህ አይነት አጋጣሚዎች በርካቶች ናቸው። በየክልሉ መራጮች፣ ሕጋዊ የምርጫ ቅስቀሳ አድራጊዎች፣ የተቃዋሚና የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች፣ የተቃዋሚ ተመራጮችና ቤተሰቦች ግንባር ቀደም የገፈቱ ቀማሾች ሆነዋል።

 

የምርጫው ሰሞን ተቃዋሚዎች በህዝብ የተሰጣቸው ድምፅ ተሰርቆም ፓርላማ መግባት አለባቸው የሚል ጭፍን አመለካከት ነበር። በሀገር ውስጥ ግን ፓርላማው የወያኔ አሻንጉሊት መሆኑን ህዝቡ አሳምሮ ስለሚያውቅ በየ ህዝባዊ ስብሰባው በደማችን ላይ ተረማምዳችሁ ድምፃችን ተዘርፎ ፓርላማ አትገቡም አለ።

 

እነ መለስ ለሕገ-ወጥ ሥልጣናቸው ሕጋዊ ሥልጣን ለመስጠት የተወሰኑ ተቃዋሚዎችን እየረገጡም፣ እየደለሉም እያስፈራሩም ወደ ፓርላማ አስገብተዋል። በዋናነት የምርጫው አብላጫ ድምፅ ማግኘቱ ሰፊ ግምት የተሰጠው የቅንጅት መሪዎችን በማሰር ብቻም አልተወሰኑም። ገና ቅንጅት በምርጫው አሸነፊ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ሕገ-ወጥ አዋጆችን ፈለፈሉ።

 

ቅንጅት አዲስ አበባን ይይዛል በማለት የኦሮሞና የአማራን ህዝብ ለማጣላት በሚል “የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ነው” አሉ፤ ቅንጅት አልተቃወመም። በ1991 ዓ.ም. የክልሉን ዋና ከተማ ወደ አዳማ ሲያደርጉ የተቃወሙ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታስረው ተደብድበዋል። ከትምህርት ገበታቸው ተባረዋል። የሜጫና ቱለማ መሪዎች ውሳኔው መስተካከል አለበት ስላሉ በሽብር ተከሰው ዛሬም እስር ቤት ናቸው። “የኦሮሚያ የባህል ማዕከልም ይገነባል፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ሀብት ትጋራለች” አሉ። ቅንጅት ደገፈው። ድርጅቱ በምርጫ ቅስቀሳው ለከተማዋ ባቡር አስገባለሁ ስላለ ለከተማዋ ባቡር ለማስገባት ፈቃዱ በፌዴራል መሰጠት አለበት የሚል አዋጅ አወጡ። ከዚህ አልፈው የከተማዋን ገቢ ለመቀነስ የመንገድ ትራንስፓርቱን እና ሌሎች አንዳንድ ተቋማትን ወደ ፌዴራል አዞሩ። በዚህም አላበቃ፤ ከቅንጅት መሪዎች መካከል ብዙዎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ናቸው በሚል “ተቃዋሚዎች በፓርላማ በኢኮኖሚ ጉዳይ አጀንዳ ማስያዝ አይችሉም” የሚልም ሕገ-ወጥ ሕግ አወጡ።

 

በአደባባይ የህዝብ ደምፅ ከመዝረፍ ጀምሮ እስከ ንፁኀን ጭፍጨፋ፣ የቅንጅቱን መሪዎች ከማሰር አልፎ ድርጅቱን አፍርሶ ስያሜውን ለፈለገው ቡድን እስከመስጠት ተሄዷል። በእነዚያ ሂደቶች ሁሉ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች አቶ መለስ እና አቶ በረከት የሚሰጧቸውን የጽሑፍና የቃል ትዕዛዝ ሁሉ ሲያስተጋቡ የነበሩ ናቸው።

 

ተቃዋሚዎች ለምን ፓርላማ አልገቡም እያሉ ሲራገሙ የነበሩ የተቃዎሚዎች ፓርላማ መግባት ውጤት አለማምጣቱን በተግባር አይተውታል። የሀገሪቱን ባንዲራ ያውለበለበ ይቀጣል ከሚል አዋጅ አንስቶ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጻረር አሸባሪ ሕግ በፀረ-አሸባሪነት ስም እስከማውጣት ሔደዋል። በሕገ መንግሥቱ የተፈቀዱ የንግግር መብቶች ተገድበዋል። ባለፈው ምርጫ ጉልህ የገለልተኛ ሚና የነበራቸው ብዙዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአዋጅና በቀላጤ እንዲዳከሙ ተደርገዋል። በምትካቸው የወያኔን ድምፅ ብቻ የሚናገሩት እንዲኖሩ እየተደረገ ነው። ፓርላማውን ጨምሮ ያለ ነፃ ተቋማት በምርጫ ተመርጦ ድምፅ ተከብሮ፣ በድምፅም መንግሥት መመስረት የሚቻልበት ሁኔታ እስከሌለ ምርጫ ማጭበርበሪያ መሆኑ ዛሬ ለመላው ሀገሪቱ ህዝብ ግልፅ ሆኗል።

 

እነአቶ መለስ የግድ ምርጫ ማድረግ ይፈልጋሉ። ለሕገ-ወጥ ዘረኛ ሥርዓታቸው የሌለ ሕጋዊ መልክ ለመቀባት ያላቸው ብቸኛ አማራጭ አድርገውታል። ከምርጫ 97 በኋላ የበለጠ የአፈና መዋቅራቸውን አጠናክረዋል። በሀገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ እንታገላለን ያሉ ተቃዋሚዎች መንቀሳቀስ አልቻሉም። ሀገር ያወቀውን ሐቅ ተናገርሽ ብለው ወ/ት ብርቱካንን ያሰሩት ያው ገና ለገና ፓርቲው ጠንክሮ ይወጣል በሚል ነው። ያልታሰሩትም በቁም እስር ላይ ናቸው። ህዝቡን ማደራጀት አልተፈቀደላቸውም። አባሎቻቸው እየተደበደቡ፣ በፈጠራ ክስ እየታሰሩ ነው።

 

የወያኔ መሪዎች ከምርጫ 97 በኋላ ሠራዊቱን፣ ደህንነቱን፣ የፌደራል ፖሊስን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስን እና እንደ አግአዚ ያሉ ልዩ ጦሮችን በአንድ የትግራይ ብሔር አባላት የበላይ አመራር ሥር አዋቅረዋል። ፍርድ ቤቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በዜጎች መብት የወያኔ መሪዎች የሚቀልዱባቸው ተቋማት ሆነዋል። የሀገሪቱን ህዝብ ሊያገለግል የሚገባው መገናኛ ብዙኀን ዛሬም የገዢዎቹ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ነው። ነፃ አስተያየት ብሎ ነገር የለም። የህዝቡ ድምፅ አይሰማም። ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት አይነት ምርጫ ማድረግ ይቻላል?

 

የአሻንጉሊቱ ምርጫ ቦርድ አሻንጉሊት መሪዎች ዛሬ በአደባባይ ብቅ ብለው ስለ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ሊነግሩን ሲሞክሩ ያሳፍራል። ጭራስ ይግረማችሁ ብለው ምርጫ ያጭበረበረን እንቀጣለን ብለው እስከመሳለቅ ደርሰዋል። ምርጫ ያጭበረበረ የሚቀጣበት ነፃ ሥርዓት በኢትዮጵያ ቢኖር ኖሮ እነአቶ መለስና የምርጫ ቦርዱ ሰዎች ወህኒ በወረዱ ነበር። ይህንን ቦርድ ህዝቡ በወሬ ሳይሆን በተግባር የወያኔ መጫወቻ ተቋም መሆኑን በቅርብ ተመልክቷል።

 

ዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ያለ ነፃ ተቋማት ምርጫ ማድረግ ጥቅሙ ለወያኔ መሪዎች ብቻ ነው። ህዝቡን አስፈራርተው ለምርጫ ካልወጣችሁ የማዳበሪያ እህል የለም፣ እናስራችኋለን፣ እንደእነ እከሌ እንገድላችኋለን ማለታቸው አይቀርም። ይሔ የሚጠበቅና ከአሁኑ የተያዘ ዘመቻ ነው።

 

በሀገራችን በነፃ መደራጀት፣ መሰብሰብ፣ ሃሳብን በነፃ መግለጽ የለም። የአፈና ሥርዓቱን የበለጠ ለማጠናከር የግንቦት 1997 ምርጫን ታሳቢ አድርጎ የወጣው እና ሥራ አጥን ሁሉ ወንጀለኛ የሚያደርገው የአደገኛ ቦዘኔ አዋጅ፤ ዛሬ “ፀረ-ሽብር” የሚል ሕግ ተጨምሯል። ወያኔ በምርጫ ዋዜማ አፈናውን ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ የታወቀ ነው።

 

አንዳንዶች የዛሬዋ ኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሠላማዊ በሆነ መንገድ መታገል ይቻላል ሲሉ እንጂ የሚቻለውን ሠላማዊ ትግል ሲመሩ አልታየም። ህዝቡም በምርጫ 97 ሠላማዊ ትግል ለማካሄድ የተዘጋጀና ይህንንም በተግባር ያረጋገጠ ነው። በሥልጣን ላይ ያለው የአፈና ቡድን ግን ለዜጎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ በጥይት አረር ምላሽ ሰጥቷል። ይሄ ባላንጣ ባለበት እንዴት ያለ ሠላማዊ ትግል እንደሚደረግ በዚህ መሰሉ ሂደት የሚደረግ ምርጫ ምንስ ውጤት እንደሚገኝበት ቢገልጹልን መልካም ነበር።

 

አንዳንድ በሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች በአቶ ልደቱ የሚመራውን ኢዴአፓን ጨምሮ ሳይጠሩ ሮጠው ወደ ምርጫ ገባን የሚሉትን ያህል ምርጫ ቦርድ ገንዘብ ይሰጣል ሲባል ያንን ገንዘብ ለመውሰድ ብቻ “ፓርቲ” የሚያቋቁሙ ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶች እንደ እነ ኦብኮ ያሉ “ፓርቲህን ከምናፈርሰው ፓርላማ ከምትገባ” ሲባሉ ሮጠው ፓርላማ በመግባት “ልባቸው” ስለታየ ዛሬም ወደ ምርጫ ግባ የሚል ተጽዕኖ ሊደግባቸውና ለዚያ ሊንበረከኩ ይችላሉ። የቀሩትም ተቃዋሚዎች የወያኔ መሪዎች ከምርጫው እንዳያፈገፍጉ የተለያዩ ዘመቻዎች ያደርጉባቸዋል። ዓላማው ምርጫ የተባለ ቴአትር ለመሥራት ስለሆነ በዚህ የተጋባዥ ተዋንያን ካባ ለብሰው መገኘት ብቻ ነው። ይህ ሁሉ መሆኑ ግን በሀገራችን ምርጫ ተደረገ አያሰኝም። ይሄ ምርጫ አይደለም።

 

የወያኔ መሪዎች አስቀድመው ኮሮጆ ቢሞሉ እንደ ምርጫ 97 ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደማይጠብቃቸው ያውቃሉ። ህዝቡ ያለ ነፃ ተቋማት የሰጠው ድምፅ እንደማይከበር አውቋል። መምረጥ እፈልጋለሁ የምመርጠው ግን ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ሲመሰረቱ፣ ነፃ ምርጫ እንጂ በማጭበርበር ለተሞላ ምርጫ አጃቢ አልሆንም ካለ ቆይቷል።

 

የኢትዮጵያ ህዝብም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያስፈልገዋል። የዚህ አይነቱ ምርጫ ቢኖር ኖሮ ዛሬ ከምርጫ 97 ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች መካከል በርካቶች አዲስ መንገድ ባልመረጡ ነበር። የሕግ የበላይነት የማይከበርበት ሀገር የሚደረግ ምርጫ የህዝብ ድምፅ የሚከበርበት ሳይሆን በህዝቡ ስም ጨቋኞች የሥልጣን ዕድሜያቸውን ማራዘሚያ እንደሚያደርጉት ደጋግመን በሀገራችን ተመልክተናል።

 

ከየትኛውም አቅጣጫ ይሁን ተቃዋሚዎችን ወደ ምርጫ ግቡ ማለት ፍትሐዊ አይደለም። የህዝብ ድምፅ ሰርቆ በሕገ-ወጥ ሥልጣን ሙጥኝ ያለው አምባገነናዊ ሥርዓት የገደላቸውን ሰማዕታት መስዋዕትነት ዋጋ ማሳጣት፣ እነዚያ ንጹኀን ላይ የተፈጸመውን ግፍ መርሳት ነው።

 

የምርጫ ቦርድ ትላንትም ሆነ ዛሬ ወያኔ እስካለ ነፃ ሊሆን አይችልም። ነፃ የምርጫ አስፈጻሚዎችም አይመደቡለትም። ይህንን የተገነዘበ ሁሉ ነፃ የምርጫ ሥርዓት፣ ነፃ ተቋማት እስኪመሰረቱ ድረስ የዚህ ሥርዓትም ምስረታ በህዝቡ የጋራ ትግል እውን እስኪሆን የወያኔ መሪዎች ባዘጋጁት የይስሙላ ምርጫ መሳተፍ አይገባም።

 

በዚህ ምርጫ መሳተፍ ለማንኛውም ህዝባዊ ወገንተኝነት አለኝ ለሚል ተቃዋሚ ፓርቲ ትልቅ ፈተና ነው። ይሄ የማያልፉት ፈተና ላይ ከመድረሳቸው በፊት እያንዳንዱን ነገር በጽሞና መመርመር ይገባቸዋል። ድምፅ የሚዘረፍበት፣ በተፈለገው ደረጃ ከሚጭበረበርበት የምርጫ ሥርዓት ምን ትርፍ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁ ለህዝቡ የማስረዳት ግዴታ አለባቸው። ካልሆነ ግን በህዝብ የመተፋትና ከጠላት ጋር እንደማበር ተደርጎባቸው ሊቆጠር ይችላል።

 

በሀገራችን ላይ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመጣ የሚፈልግ ማንኛውም በሀገር ውስጥ ይሁን በውጭ ያለ ወገን የሚያደርገውም እንቅስቃሴ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚወስዱት ነፃ ተቋማት የሚመሰረትበትን ሥርዓት ለመመስረት የሚደረገውን ትግል መደገፍ ነው።

 

ዛሬ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስረዳው ፍፁም ያፈና ሥርዓት መንገሡን እንጂ ምርጫ የሚደረግበት ነፃ የውድድር ሜዳ አለመኖሩን ነው። ስለዚህም ነው ከዚህ ቀደም እንደነበረው ህዝቡ እየተገደለ፣ እየታሰረና እየተገረፈ በድፍኑ ወደ ምርጫ ግቡ የሚል ድፍን አስተያየት አድማጭ ከማግኘት ይልቅ ለትዝብት የሚጥል ድምዳሜ የሚሆነው።

 

የእነአቶ መለስ አስተዳደር የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችን እንደ ግል ራዲዮ በፈለጉት ሰዓት እየከፈቱ የመሰላቸውን ሊያስለፈልፏቸው ይችላል። የቦርዱ በየትኛውም ደረጃ ያለ ኃላፊ ያለውን የይስሙላ ሥልጣን የማያውቅ የለም። ከላይ ዝቅ ሲባልም ገለልተኛ ሊሆኑ ቀርቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት በግልፅ የወያኔ አባላት መሆናቸው የሚታወቁ ግለሰቦች ጭምር ነው።

 

በቀጣዩ ዓመት የሚደረገው የይስሙላ ምርጫ ሊያሳስበን አይገባም። ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀ ነው። ወያኔ ራሱ አስመራጭ፣ ምርጫ ተወዳዳሪ፣ ድምፅ ቆጣሪ፣ ቅሬታ ሰሚ ነው። ስለዚህ ሳይወዳደርና ህዝብ ሳይመርጠው አሸንፏል። ሊያሳስበን የሚገባው እንዴት ባለ ፍጥነት እውነተኛ የምርጫ ሥርዓት በሀገራችን ይመሰረታል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ፤ ብሎም ወደዚያ ጎዳና የሚወስደውን ሁሉን አቀፍ ትግል ማድረግ ነው።

 

ከዚያ ውጭ በይስሙላ ምርጫ መሳተፍ በምንም መንገድ የዲሞክራሲ ሂደትን አያመጣም። አያዳብርም። በተጭበረበረ ምርጫ የዳበረ ዲሞክራሲ የለም። የብዙ የተጭበረበሩ ምርጫ ውጤቶችም አንድ እውነተኛ ምርጫ አይወልድም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ