የኃይማኖት ወይስ የፖለቲካ ቀውስ (እውነቱ ዘገየ)
እውነቱ ዘገየ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
“ሕመሙን የደበቀ ፈውሱን ደበቀ” እንደሚባለው የችግሮቻችን መንስዔዎች በቅጡ ተለይተው መታወቃቸው ድልን የመቀዳጀት ያህል የሚፈጥርብን ደስታና ስሜት ባይፈጥሩልንም ውለው አድረው የሚያመሩን ወደዛ ሃሴት ነው። ቅድስት ቤ/ያን ለዚህ ቀውስ የዳረጋትን የችግሮችዋን መንስኤዎች ቀጥተኛ በሆነ መልኩ (መንገድ) ከግላዊ አጀንዳዎችንና አስተሳስባችን ርቀን ጭብጥ ባላቸው መረጃዊ በሆነ ውይይት እንደ ባለ አዕምሮ በጭዋነት መንፈሥ በመጠባበቅ አንስተን መወያየቱና ለመፍትሔ መደማመጡ ዘለቄታ ያለው ሠላምና እረፍት ያመጣል የሚል እምነት አለኝ።
በማስቀደም በአሁኑ ሰዓት በቅድስት ቤተ-ክርስቲያናችን ለተፈጠረው ወቅታዊ መቆራቆስ የተሰማኝን ከፍተኛ ኀዘን ለመግለጽ ስወድ ይህን ጽሑፍ የማንብብ አጋጣሚ ላጋጠማችሁ በቅርብም በሩቅም ለምትገኙ የቅድስት ቤ/ያን ልጆች ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋና ምህረት ሠላምም ይሁን እላለሁ።
“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር ኃይማኖታዊ ወይስ ፖለቲካዊ ቀውስ ነው ይላሉ?” በሚል ርዕስ የበኩሌን ለመፃፍ የተገደድኩበት ዋና ምክንያት ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ ጉዳዩን አስመልክተው ከተለያዩ ዓይነት ሰዎች የተለያዩ ገንቢና አፍራሽ ሃሳቦችን በተለያዩ ድረ ገጾች በማንበቤ ነው። ነገሩ አቅጣጫውን ስቶ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እያመራ እንዳለ በመረዳት፤ አበው “ውሃ ከምንጩ፣ ነገር ከባለቤቱ ሲሆን ይጥማል” እንዳሉት ይህን ጽሑፍ እንደ እግዚአብሔር ሰው እንደ መንፈሣውያን ለሚያስቡና ለሚመላለሱ ለእግዚአብሔር ልጆች ለመልካም ነገር ይተጉና በሮቻቸውንና ጆሮቻቸው ከጠላት አሠራር ይጠበቁ ዘንድ አዘጋጀሁት።
ለመሆኑ በቤተ-ክርስቲያን መካከል ችግር ይፈጠራል ወይ …? የብዙዎች “ኑ በአምላካችን በእግዚአብሔር ቤት ዘላለማዊ ሠላምና ዕረፍት አለ …” እያልን ከምንሰብካቸውና የምስራች የሆነውን ወንጌል ከምንነግራቸው በውጭ ካሉ ሰዎች የሚሰማና የሚነሳ ተገቢ ጥያቄ፣ ለምን? ሠላምን ታገኛለህ ታርፋለህ ብሎ የሚናገርና የሚሰብክ ሰው አስቀድሞ ራሱ ሠላምና ዕረፍትን የተላበሰ ሰው ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታልና።
በቤተ-ክርስቲያን መካከል ለሚፈጠረው ማንኛውም ዓይነት ችግር ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ተጠያቂ አይደለችም በማለት ሐተታየን ጀመርኩ። በመቀጠልም የቤተ-ክርስቲያን ባለቤትና መሥራች ስህተትና ህጸጽ የማያውቀው እግዚአብሔር ነው አልኩ። ስቀጥል ደግሞ ቤተ-ክርስቲያን እግዚአብሔር አምላክ በአንድያና ተወዳጁ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ንጽኅ ደም የመሠረታት የሠማያዊት ኢየሩሳሌም ተምሳሌት እንጂ መዘጋጃ ቤት ወይንም የቀበሌ ፍርድ ሸንጎ ክፍል አይደለችም በማለት ለዛሬ ያዘጋጀኋትን ጦማር በመግብያዬ አሰፈርኩ።
በቤተ-ክርስቲያን መካከል ለሚፈጠረው ትልቅም ትንሽም ችግር ተጠያቂው እግዚአብሔር ሳይሆን በአደራ በተሾሙት ግለሰቦች ሥጋዊ ፍቃድና ምኞት ተከትሎ የሚመጣውን ራስን የአለመግዛት ውጤት ነው የሚል ጽኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነቴ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእምነት ለወለደው ለመንፈሣዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈው በመጀመሪያይቱ መልዕክቱ ምዕራፍ ስድስት፣ ከቁጥር አራት ጀምሮ እንደጻፈው በቤተ-ክርስቲያን መካከል ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ሳይደብቅ በመግለጽ፤ የችግር ፈጣሪዎች ማንነትና መገለጫ ባህሪ (ስብዕና) አክሎም አስፍረዋል። ሙሉ የቃሉ ይዘት እንዲህ ይላል፦
“ከእነዚህም ቅንዓትንና ክርክርን፣ ስድብም፣ ክፉ አሳብም፣ እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፤ አዕምሮአቸውም በጠፋባቸው፣ እውነትንም በተቀሙ፣ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፍያ የሚሆን በሚመስላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉ ራቅ።”
በዋናነት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ ለማሳየት የፈለገው ከዚህ ከተጻፈው አምላካዊ ቃል በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በቤተ-ክርስቲያን ለሚሆነው (ለሚፈጠረው) ኢ-ክርስቲያናዊ የሆኑ ተግባሮች፤ ማለት እርስ በርስ መናቆርና መባላት የመሰሉ አስቀያሚ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ከእግዚአብሔር ልጆች የሚጠበቅ የሕይወት ፍሬ ሳይሆን፤ እግዚአብሔር አብ ያልተከላቸው በጊዜው ደግሞ የሚነቅላቸው የተጠሩትን ሠላምና ዕረፍት ብሎም ትርፋማ ሕይወት አይተው ሳይጠሩ ተድበስብሰው በቀላዋጭነት የሚኖሩ፣ በመስኮት የተቀመጡ፣ በተከፈለ ልብ የሚመላለሱ፣ በልባቸው በሸፈቱ ምናምንቴዎች የሚፈጠር ነው በማለት ጢሞቲዎስን ሲያረጋጋው እንመለከታለን።
ዛሬ ተፈጠረ የሚባለውን ችግር አንስተን ስናወራ አብሮ ደግሞ ስማቸው ጎልቶ የሚታወቀው የቤተ-ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ማንነት (ስብዕና) በዚህ አምላካዊ ቃል መመርመሩ ድፍረት አይመስለኝም። የእግዚአብሔር ቤትንና የእግዚአብሔር ህዝብ እያወኩና እያበጣበጡ ያሉ ግለሰቦች እውነት ሁሉን የሚያውቅ ሰማይ ዙፋኑ፣ ምድር የእግሩ መርገጫ የሆነ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ህዝቡን ይመሩና ያስተዳድሩ ዘንድ የጠራቸው ካህናት ናቸው? ወይስ ሰዎች ለፖለቲካ ጥቅማቸው የቀቡዋቸው ወታደሮች? እግዚአብሔር በመንገድ ሁሉ ጻድቅ ነው። ደግሞም በዘመናት ሁሉ የተበተነውን ለመሰብሰብ የወደቀውን ለማንሳት የተሰበረውን ለመጠገን ተስፋ ያጣችውን ነፍስ በአዲስ ጎዳና በሕይወት ለማኖር አገልጋዮችን ላከ እንጂ ህዝቡንና ቤቱን ለማበጣበጥና ለማወክ ሰዎችን አልጠራም፤ አገልጋዮችን አላከም።
ሐዋርያው ያዕቆብ በመልዕክቱ ምዕራፍ አራት ቁጥር አንድ ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፦
“በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምኞቶቻችሁ አይደሉምን?”
እንደ ተልባ መንጣጣቱ፣ አጉል ጥብቅና መቆሙ፣ መነታረኩ ለጊዜው ይቅርና፤ ለዚህ ጥያቄ (ለሐዋርያው ያዕቆብ ጥያቄ) የሚኖርዎት ምላሽ ምን ይሆን? በምንስ ለማመካኘት ይሞክሩ ይሆን? ማስተባበያ ቃልዎስ ምን ይሆን? አንድ የሚሉት ቃል ይኖርዎት ይሆን? በቤተ- ክርስቲያን ለሚፈጠረው ችግር ከዚህ የተለየ ምክንያት ይኖሮታል?
የተወደዳችሁ የቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ልጆች፣ ሠላም ወዳድ ምዕመናን የምናመልከው አምላክ እግዚአብሔር አይዘበትበትም! ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ እንደ ሞኝነት በሚያስቆጥር ቃል ማንም አያታልላችሁ! ለማለት እወዳለሁ። ሰው ስለ እግዚአብሔር ቤት እና ስለ እግዚአብሔር ህዝብ ከእግዚአብሔር በላይ ሊያስብ አይችልም። የሚቃጣው የተገኘ እንደሆነም ውሸት ነው።
ሰዎች ግላዊና ሥጋዊ ግጭቶቻቸው ኃይማኖታዊ ግጭት ለማስመሰል ፖለቲካዊ ቅራኔያቸውን ኃይማኖታዊ ቅርጽ ለማስያዝ በሚያደርጉት ፍልሚያና ግብግብ ለምን ደምህን ደመ ከልብ ታደርጋለህ? አንዳንዶች የተመኙትን አግኝተዋል። ከተሾሙ ጥቂት ጊዜያቸው በመሆኑ ምኞታቸው በየመገናኛ ብዙኀን ስማቸውንና ፎቶ ግራፋቸው ማስተዋወቅ ነበርና እንዳሰቡት ተከናወነላቸው። ተሳካላቸው። ሌላ የሚታወቁበት እውቀትና ጥበብ የላቸውማ! ወዳጄ ጊዜዎንና ጉልበትዎን መስዋዕት አድርገው የገጠሙት ሙግትና እያፋፋሙት ያለውን እሳት እውነት በእውነተኛ መንፈሣዊ ቅናት የቤተ-ክርስቲያን ጉዳይ ግድ ብሎት ነው ወይስ በሥራ ብዛት የተወጠረውን አዕምሮ አልያም በቤተሰብ ናፍቆት በሃሳብ የተያዘውን ህሊና አጋጣሚውን በመጠቀም ለመዝናንት ያህል ነው? በተለያዩ ድረ ገጾች ከይመለከተናል ባዮች ቁጥራቸው የማይናቅ ወገኖች መሰል አስተያየቶችን ማየት ስለቻልኩ ነው።
ታድያ ግድ የሚልዎት የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከሆነ አንዱን በመደገፍ፤ ሌላውን ከማጥላላትና ከመወረፍ ከመንፈሣውያን ሰዎች የማይጠበቁ ፀያፍ ቃላቶችን አለቦታቸው በመጠቀም ለቤዛ ቀን የታተመውን በውስጣችን የሚኖረው የእግዚአብሔር መንፈሥ ከማሳዘን ይልቅ ሠላም እንደሚሻና እንደተጠማ የእግዚአብሔር ሰዎች በአንድ ድምፅ የችግሩን መንስዔ ለማወቅ መጠየቅ በተገባ ነበር። የዓለማውያን መዝናኛ ቃላቶችን እያነበብን ጠፍተን ለማጥፋት ከምንተጋ።
የእግዚአብሔር ሰዎች ለዓለም መልዕክት ሰጪዎች እንጂ ከዓለም ተቀብለው መንፈሣቸውን የሚረብሹ ወንድሞቻቸውን የሚያናጉ፣ ቤቶቻቸውንም የሚያውኩ አይደሉም። እውነት ከማይጠፋ ዘር ከተወለድክ ከራስህ አልፈህ ስለሌላው የምታውቀው በእግዚአብሔር መንፈሥ እንጂ በከበሮ መቺዎች ልሣን አይደለም። ራስን መመርመር ተገቢ ነው፣ ስለምትናገረውና ስለምትጽፈው ነገር ተጠያቂ ነህና! መዓቱም ለልጅ ልጅህ ነው። ቀልድ አይደለም ሽንጥህን ገትረህ እየተከራከርክበት ያለኸው ርዕስ የእግዚአብሔር ስም አንስተህ ነው። ስለ እግዚአብሔር ቤት ነው እየተከራከርክ ያለኸው። የክርስትና አምላክ ስንፍናን የሚጠላ አምላክ እንጂ ስንፍናን የሚያበረታታ አምላክ አይደለም። ከስንፍና የተነሳ ደግሞ በራስህ ላይ ፍርድን ታከማቻለህ እንጂ ምህረትን አታገኝም።
እግዚአብሔር ፈታሔ ነው፤ ይሉኝታ ይዞት የሚቀለብሰው ፍርድ አይኖርም። ይህን ማወቃችን ከዛሬ ጀምሮ በእግዚአብሔር ስም የምንሠራቸውን የድፍረት ኃጢአት የአመጻ ሥራዎችን ገደብ እናበጅለታለን። ብርሃን ከጨለማ ህብረት እንደሌለው ሁሉ እግዚአብሔር ከሰዎች ዓመጽ ጋር ምንም ክፍል የለውም። በቤተ-ክርስቲያን መካከል ያለ እውቀት የምናደርጋቸው ማናቸውም ዓይነት ተሳትፎዎች እግዚአብሔር የለበትም። ቅናቱ ካለን እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች ከመንቀፍ በመታቀብ እውቀቱ ካላቸው ሰዎች ተጠቃሚዎች ለመሆን መንፈሣችንን ማዘጋጀት፣ ልባችንን በቅንነት መስጠት ይጠበቅብናል። እያደረግኩት ያለሁት ተግባር፣ እየሠራሁት ያለሁት ሥራ እግዚአብሔር የሚከብርበት ቤተ-ክርስቲያን የምትጠቀምበት የእግዚአብሔር ህዝብ የምያርፍበት የሚሳርፍ ነው ወይ? በማለት ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል፤ ራሳችንን በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ሰዎች ትዝብት ከመጣላችን በፊት።
የምንሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት አይደል? ዋጋችንን ከእግዚአብሔር ለመቀበል አይደለምን? ታድያ ሥራችን ከእግዚአብሔር የሚያራርቀን ሆኖ ከተገኘስ? የምንሠራው ሥራ ለማን ነው? መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው። ሰው አይደርስብኝም በማለት የብዕር ስም በመጠቀም ብትጽፍም አድራሻህ ከቶ ሁሉን ከሚያውቅ ከልዑል እግዚአብሔር ህልውና የተደበቀ አይደለም። የመዘንጠል አመል ያለው የልብን የሚያደርሱ ብዙ መወያያ ርዕስ ያላቸው መድረኮች አሉ። እዛው በመገኘት እስኪወጣሎት ድረስ መፏነን ይችላሉ። ከዘላለም ፍርድ ለማምለጥ ባይችሉም በሥጋ ዘመንዎ እንደሆነ እግዚአብሔር በምህረቱ ብዛት ያኖሮታል።
አሁንም በድጋሚ ላሰምርበት የምፈልገው ነጥብ ቢኖር፤ በበል ልበልህ እና በቃላት ብዛት የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ በመረዳት፣ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ልጅ የችግሩን መንስዔ ራሱን ችሎ ከማናቸውም ተጽዕኖዎች ራሱን በማንጻት ለማወቅ ጥረት ቢያደርግ ድምፁን በአንድነት ቢያሰማ የተሻለ ነው እላለሁ። ለምን? ዘመኑ ሰው እውነቱ ሲነገረው ስላልደረሰበት እውነት ግራ ቀኙን አይቶ በማስተዋል ከመናገር ይልቅ የተነገረውን ሃሳብ ውሸት ሰውየውን ወንጀለኛ ማድረግ ስለ ሚቀናው ነው።
ለዚህም ነው እላለሁ ብዙ የቤተ-ክርስቲያናችን ሊቃውንት መምህራን ደቀ-መዛሙርት የእግዚአብሔር ሰዎች ብዙ ከማለት የተቆጠቡ። ማን በሰነፍ በትርና ምላስ መገረፍ ይወዳል ብላችሁ ነው? አዎ! ልባችሁን ስታሰፍሉን የምንላችሁ ነገር ይኖራል። ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ አበክሮ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ ዘራቸውን አለ ቦታው፣ አለ ጊዜውና አለ አግባብ እንዳይዘሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው። ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለው እንዲህ ነው፤ “በጎቼ ያውቁኛል፣ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ድምጼንም ይሰማሉ ይከተሉምኛል።”
ይህንን ጽሑፌን ለማገባደድ ያህል ብከብድባችሁም በቅድስት ቤተ-ክርስቲያናችን የተፈጠረው ችግር ምንም ዓይነት አስተምህሮአዊም ሆነ አስተዳደራዊ ችግር አለመሆናቸው እና ችግሩም ለውስጥ አዋቂዎች አዲስና እንግዳ እንዳልሆነ ለመንፈሣውያን የቤተ-ክርስቲያን ልጆች ለመግለጽ እወዳለሁ። በሚቀጥለው ጽሑፌ በስፋት ከምንመለከታቸው ዝርዝር ሃሳቦች በከፊል ለማስተዋወቅ ያህል ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በመጀመሪያይቱ ጢሞቲዎስ 6፤4 መሰረት፤ የአድዋ ተወላጅ “አባ” ጳውሎስም ሆኑ በእንጀራ ስማቸው የሚታወቁ የሽሬ ተወላጁ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት “አባ” ተከስተ በመጀመሪያ እነዚህ ግለሰቦች እውነት እግዚአብሔር የጠራቸው ካህናት ናቸው ወይስ የፖለቲካ ሰዎች ለፖለቲካ ጥቅማቸው የሾምዋቸው ወታደሮች ናቸው?
ቀጥሎ ደግሞ ዘመናት ያስቆጠረ የተብላላ ጊዜንና አጋጣሚን የሚጠብቅ በፖለቲካ መሪዎች በተለይ በአድዋ ተወላጆችና እና በሽሬ ታጋዮች መካከል ያለውን ያለመግባባት፣ የመቃቃር መንፈሥም መዘንጋቱ የዋህነት ይመስለኛል።
ትናንት ብብዙ ምልጃና ፖለቲካዊ አጋጣሚ የተሾመ “አባ” ተከስተ ለምን በ“አባ” ጳውሎስ ላይ ሊያምጽ ቻለ? ለመሆኑ “አባ” ተከስተ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ሙሉ ሰው ነው ወይ? ካሜራ አዳኙ “አባ” ተከስተ የቅድስት ሥላሴ መንፈሣዊ ኮሌጅ ደቀ-መዛሙርት የአስተዳደር ችግር አለብን በማለት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ለምን መፍትሔ አልሰጠም? ዛሬ ነው ረዳት ፓትሪያሪክ መሆኑ የነቃ ወይስ ለተሾሙበት ዓላማ የሚቆሙበት ጊዜና ሰዓት በመድረሱ ነው?
“በአባ” ተከስተ እና አብሮአቸው ከተሾሙት ሌሎች ሁለት “መነኮሳት” መሾም ያልተስማሙ የትግራይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ መርሃ ክርስቶስ ለምን እነዚህ ሰዎች ከተሾሙ ቆቤን አነሳለሁ እስከ ማለት ደረሱ? አቡነ መርሃ ክርስቶስ የ“አባ” ተከስተ ሹመትን የተቃወሙበት ዋና ምክንያታቸው ምን ነበር? በማንና በምንስ ነጥብ አቡነ መርሃ ክርስቶስ ከጽኑ አቋማቸው ሊመለሱ ቻሉ?
“አባ” ተከስተ እውነት ተቆርቋሪ፣ ቤተ-ክርስቲያን የማስተዳደር ችሎታና መፍትሔ የማምጣት አቅም ቢኖረው ራሱን ችሎ የቆመ ዓይነት ሰው ቢሆን ኑሮ የቅድስት ሥላሴ መንፈሣዊ ኮሌጅ ደቀ-መዛሙርት የአስተዳደራዊ ችግር ጥያቄ ሲያቀርቡ ጥያቄውን ወደጎን በመተው በምርጫ ባልተሳካላቸው በቅንጅት አባላት ቤተ-ክርስቲያንን ለመረበሽ የተመከረ ምክር ነው ሲሉ የተደመጡ ለምንድን ነበር?
ነፍሳት እንደ ቅጠል ሲረግፉ ደማቸው ሳይደርቅ (የጅማ ነዋሪዎች) ወንድም እህቶቻችን የቀብር ሥነ-ሥርዓት ሳይፈጸም ከገዢው ፓርቲ ጎን በሞቆም “እስላምና ክርስቲያን አንድ ነው፤ በአካባቢው ምንም ዓይነት ኃይማኖታዊ ችግር አልተፈጠረም” በማለት የተሰጠውን ወረቀት ያነበበና የተሾመበትን አደራ የፈጸመ ነፍሰ ገዳይ አይደለም ወይ “አባ” ተከስተ ማለት?
የፈረንጁ ቀይ አፈር ረግጦ በመምጣቱ ብቻ የተሾመ “አባ” ተከስተ የመልካም አስተዳደር ታጋይ ከሆነ በአዲስአበባ ሀገረ ስብከት የጋዜጣ ክፍል ዋና አዘጋጅ ሆነው ያገለግሉ የነበሩ ቅድስት ቤተ-ክርስቲያናችን ካፈራቻቸው ወጣቶች ሊቃውንት መምህራን አንደበተ ርቱዕና ባለ ቅኔ መ/ም ተመስገን ያለአንዳች ማስጠንቀቅያ በአዘጋጁነት በሚመሩ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ የሰፈረው የአዘጋጁ እምነትና የቤተክርስቲያን ጥቅም ማዕከል ያደረገ ጽሑፍ ለወያኔ መንግሥት የማይመች ሆኖ በመገኘቱ ሀገር ሠላም ነው ብለው የቢሮ ሰዓታቸውን ጠብቀው በሚገቡበት ሰዓት ከሥራ ገበታቸው ሲታገዱ ለአላስፈላጊ የሕይወት ዋስትና የሌለው ሕይወት ሲዳረጉ “አባ” ተከስተ ምን ይጠብቅ ነበር? ይሄ ነው የመልካም አስተዳደር መርኅ?
“ጠርጥር በገንፎ ውስጥ አይታጣም ስንጥር።” ለምን? በመንፈሣዊ ዓለም ውስጥ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚል መርኅ ቦታ የለውምና። ምንም እንኳ “አባ” ጳውሎስ ከተጣለባቸው ኃላፊነት አንጻር በሥራቸው ምንደኛ ሆነው በመገኘታቸው ተቋውሞአችንን ብናሰማ፤ “አባ” ጳውሎስን የተቃወመ ሁሉ ግን የቤተ-ክርስቲያን ወዳጅ ነው ማለት አይደለም። ተቃዋሚ አካል ወይም ግለሰብ የተቃውሞው ነጥብ ምንድን ነው? ለመሆኑ እርስዎ አባ ጳውሎስን የሚቃወሙበትን ነጥብ በተጨባጭ ለማስቀመጥ ይችላሉ? እንግዲያውስ አስቀድመው ነጥቦችን በማስታወሻ ደብተርዎን ለማስፈር ይሞክሩ በመቀጠል ደግሞ “አባ” ጳውሎስን ከተቃወሙበት ነጥብ የፀዳ ነው የሚሉት ግለሰብ ወይንም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት ድርጅት በ”አባ” ጳውሎስ ላይ ያሰማውን (የሚያሰማውን) የተቃውሞ ነጥብን በተመሳሳይ መልኩ በማስታወሻ ደብተርዎ ለማስፈር ይሞክሩ። ይህን ካደረጉ በእውነት ድምፅዎንና ልፋትዎን አንድ ቀን ዋጋ ይኖረዋል። ይህ ሁሉ ልፋትዎ ግን በስሜት በስሚ ስሚና በአጉል ድፍረት የሆነ እንደሆነ ግን ለመገንባት ያመቻቹትን ለማፍረስ ያዘጋጁትን እንደሆነ አይዘንጉ። የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት “አባ” ተከስተ “አባ” ጳውሎስን በመቃወማቸው ብቻ በምንም ዓይነት መልኩ “አባ” ተከስተን የምንደግፍበት ምንም ዓይነት ተጨባጭና አሳማኝ ነጥብ የለንም።
“ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል፣ ሲካፈል ይጣላል” እንዳሉት ነው ቁምነገሩ። በተንኮልና በክፋት ተረግዘው በአመጻ የተወለዱ የአጋንንት መነሃርያ የሰይጣን ማኅበር “የማኅበረ ቅዱሳን” ድርሻም መዘንጋት የለብንም። መቼም ሐበሾች ስንባል መርዝ ይገድላል እየተባልን እንኳ ካልቀመስኩት ማለት ነው የሚቀናን። ይሁን እና ጓዳችን ካልገባ በቀር ጥፋቱና ኃጢአቱ አልታይ ያለን የሰይጣን ማኅበር ከግድግዳ የመላተም ያህል እንዳይከብደው ትናንት የውጪውን ለማዳከም በሀገር ውስጥ ከሚገኘው ሲኖዶስ በመጣበቅ ከእናንተ ጋር ነን በማለት በውጭ የሚገኙትን አባቶች ስምና ዝና በማጉደፍ እፎይታ ተሰምቶት ሲያበቃ፤ ዛሬ ደግሞ እንደገና ጉልበቱን አድሶ ከላይ የተመለከትናቸውን አበይት ነጥቦችን ሌሎች እንደ መግቢያ ቀዳዳ በመጠቀም በአባቶች መካከል የሃሳብ መለያየት በማምጣት ለዚህ ዳርጎናል።
የተወድዳችሁ የቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ልጆች እነዚህንና ሌሎች አንኳር አንኳር ነጥቦች ይዤ ልቦናችሁን ያሰፋችሁልኝ ያህል በድጋሜ መፍትሔን የሚጠቁሙ ሃሳቦችን ይዤ የመጨረሻ በሆነው በሚቀጥለው ጽሑፌ እስክንገናኝ ድረስ የእግዚአብሔር ሠላም ከሁላችን ጋር ይሆን ዘንድ የዘወትር ፀሎቴ ነው።
የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ሀገራችንና ቤተ-ክርስቲያናችን ይጠብቅ! ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ያገናኛል!
እውነቱ ዘገየ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



