ክርስቲያን ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

የምርጫ 2002 ዕቃ ዕቃ ጨዋታ ተጠናቀቀ። ከእባብ ዕንቁላል የእርግብ ጫጩት የጠበቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተደናግጠው የሚሉትን አጥተው ዝምታን መርጠዋል። አቶ መለስ ዜናዊ በሠላማዊ መንገድ ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆኑን ለማወቅ ምርጫ 1997 ወይም ምርጫ 2002 አስፈላጊዎች አልነበሩም (ይህ የኔ የግል አስተሳሰብ ነው)። የአቶ መለስ ዜናዊን አምባገነንነት እስከ አሁን ያልገባው ካለ አውቆ የተኛ መሆን አለበት።

 

አምባገነን መሪዎች ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሆነው አያውቁም። እናም አቶ መለስ ዜናዊ በምርጫ ሂደት ሥልጣን እንዲለቅ መጠበቅ የለብንም። ይህንን ስል በምርጫው ሂደት ማለፍ አስፈላጊ አልነበረም ለማለት አይደለም። የምርጫው ሂደት አቶ መለስን ከሥልጣን ማውረድ ባይችልም እንኳን ሌሎች ጥቅሞች ነበሩት፦ ህዝብ ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲወያይ ዕድል መክፈቱ አንዱና ዋነኛው ጥቅሙ ነው። ከዚያም አልፎ ቢያንስ በሠላማዊ መንገድ (በምርጫ) ብቻ መታገልን እንደመፍትሔ የቆጠሩ ሰዎች ይህ መንገድ ለአቶ መለስ እንደማይሰራ እንዲገባቸው ያደረገ ይመስለኛል። እናም አማራጭ መንገዶችን እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ይመስለኛል። ይህንን ስል ግን ጦርነትን እንደ አማራጭ ማቅረቤ አይደለም። በጦርነት እና በምርጫ መካከል ያሉ ሌሎች የትግል መንገዶች አሉ።

 

በምርጫ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለው ሲያስቡ የነበሩት ፖለቲከኞቻችን አሁን ፊታቸውን ወደ ሌላ የትግል አቅጣጫ ማዞር ይጠበቅባቸዋል። የአቶ መለስ ዜናዊ ድራማ ተዋንያን መሆን ሊበቃቸው ይገባል። ሌላ አምስት ዓመት ጠብቀው ሌላ ድራማ ለመተወን (በሌላ የምርጫ ድራማ ለመሳተፍ) ባይሞክሩ ደስ ይለኛል። ዲሞክራሲ ሂደት ነው፤ በአንድ ምርጫ ለውጥ መጠበቅ የለብንም ማለታቸውን አቁመው ሌላ የትግል ሥልት ይቀይሱ። አሁንም ቢሆን የምርጫውን ሂደት ወደ ፍርድ ቤት እንወስዳለን ማለታቸውን ያቁሙ። አቶ መለስ ሌላ ድራማ አዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል። ፍርድ ቤቱ በአቶ መለስ ትዕዛዝ እንደሚሠራ እያወቁ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ትርጉም የለውም። እኔ ይህንን እንደ ጅልነት ነው የምቆጥረው። ነፃ ፍርድ ቤት፣ ነፃ የመገናኛ ብዙኀን፣ ነፃ የጦር ሠራዊት፣ ነፃ የፖሊስ ኃይል በሌለበት ሀገር ነፃ ምርጫን መጠበቅ ቂልነት ነው። እናም በምርጫ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚለው አመለካከት ሊያከትም ይገባል።

 

መለስ ተቃዋሚዎችን ሥልጣን ለማጋራት እንደሚያስብ ለዚህም በሽማግሌዎች በኩል ድርድር ማስጀመሩን ጭምጭምታም ቢሆን እየሰማን ነው። ይህም ቢሆን ከድራማነት ያለፈ ትርጉም የለውም። ሽማግሌዎቹም ቢሆን ራሳቸውን ባያቀሉ ጥሩ ነው። በተለይም እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ ያሉ የህዝብ ፍቅር ያላቸው ሰዎች “የሽማግሌ ቀላል” ከመባላቸው በፊት (እስከ አሁን ካልተባሉ) ራሳቸውን ከዚህ ሂደት ቢያወጡ መልካም ነው። የባለፈው ሽምግልናቸው አንዲት ንፁኅ ነፍስን በእስር ቤት እንድትማቅቅ ከማድረግ በስተቀር ያተረፈላቸው ነገር የለም። ይህ ጠባሳ እያለ ሌላ የሽምግልና ሂደት ለመጀመር ማሰባቸው የሚያስቅ ነው። እርግጥ ነው ብርቱካን በቅርብ ግዜ ልትፈታ እንደምትችል ግምቴ ነው። ይህንንም ከምርጫው በፊት በተለያዩ ድረ ገፆች ባሰፈርኩት ጽሑፌ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። የብርቱካን የመታሰር ነገር ከምርጫ 2002 ድራማ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ከምርጫው በኋላም እንደምትፈታ “መጪው ምርጫ እና የብርቱካን ሚደቅሳ የመፈታት መቼት” በሚል ርዕስ በፃፍኩት ጽሑፍ ላይ አስፍሬ ነበር። ብርቱካን የታሰረችው የአቶ መለስን የምርጫ 2002 ድራማ ታበላሻለች ተብሎ ነው። ካሉት ተቃዋሚ መሪዎች የህዝብን ቀልብ መግዛት የምትችል እርሷ ስለነበረች።

 

የምርጫ 2002 ድራማ መጠናቀቅን ተከትሎ አቶ መለስ፤ ብርቱካን እንድትፈታ ይፈቅዳል። ሽማግሌ ተብየዎቹም የዚህ ድራማ ተዋናይ በመሆን ብቅ ማለታቸው አይቀርም። አቶ መለስ እኛን ሰምቶ ብርቱካንን ፈታ ማለታቸው አይቀርም። ሁሉም ነገር በአቶ መለስ ዜናዊ ፈቃድ ብቻ የሚከናወን መሆኑን ግን ልብ ይበሉልኝ። ይህ ደግሞ የአምባገነንነት መገለጫ ነው።

 

እናም አቶ መለስ ዜናዊ የሚጽፋቸውን ድራማዎች መተወን አቁመን፤ የራሳችንን ድራማ ጽፈን፤ የራሳችንን ታሪክ ሠርተን አምባገነንነትን ልናስቆም ይገባል።


ክርስቲያን ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ